
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከጥር 1/2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳስታወቁት በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የተከሰተው በንግድ ሥርዓቱ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመኖራቸው ነው፡፡
በቂ ምርት እንዲያቀርቡ ትስስር የተፈጠረላቸውም ይሁኑ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፍትሐዊ አሠራርን ተከትለው አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተመላክቷል፡፡ ይህ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የሚኒስቴሩ መዋቅሮችና ሌሎች አጋር የመንግሥት አካላት ክትትልና እርምጃ ዝቅተኛ መሆኑን እንደተረጋገጠ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋትና በከተሞች በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ 624 ሺህ ኩንታል ስኳርና 600 ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄት በመንግሥት ድጎማ በጀት ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከመንግሥት ስንዴ ወስደው ዱቄት የሚያከፋፍሉ 400 የዱቄት ፋብሪካዎች አሉ፤ ከነዚህ ውስጥ ከ300 በላይ ለሚሆኑት የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡
የንግድ ሂደቱ በሕገ ወጥ ደላሎች የተተበተበ በመሆኑ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን ነገር በቀላሉ እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ እንደ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች የፍራፍሬ ውጤቶችን እሴት ሳይጨምሩ እስከ ሰባት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ እንደተደረገባቸውም አቶ ወንድሙ ፍላቴ ተናግረዋል፡፡ የምርት አቅርቦት የሌለ አስመስለው የሚከዝኑ፣ የሚደብቁና በመነጋገር ያሻቸውን የዋጋ ተመን እያወጡ ሕጋዊ ባልሆኑ ነጋዴዎችና ደላሎች እየተፈፀመ ያለው ድርጊት የዋጋ ንረቱ ዋነኛው መንስኤዎች እንደሆኑም ነው ያመለከቱት፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት እየሠራ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ጊዜያዊና ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙም ተገልጿል፤ ግብረ ኃይሉ ከሁሉም ክልሎች አጋር አካላት መንግሥታዊ መዋቅሮች የተውጣጣ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በአዲስ አበባ አስተዳደር 74 ሺህ 404 የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን ለኢብኮ ገልጿል፡፡ እርምጃው የተወሰደው 105 ሺህ 693 ተቋማት ላይ በተደረገ ምርመራ የንግድ ድርጅት የማሸግ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ሥራ ፈቃድ ማገድና መሰረዝ እና ከትስስር የማስወጣት እርምጃ መወሰዱን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡ ሕገ ወጥ ደላሎችን ከገበያ ለማስወጣት፣ ምርቶች በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ወደ ሸማቹ የሚደርሱበትን መንገድ መፍጠርና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ይሠራል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ