“ኢትዮጵያ ከዘላቂ ጥቅሟ አንጻር የራሷን አማራጭ በመጠቀም የተከፈተባትን ዘመቻ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይጠበቅባታል” በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር

120
ጎንደር፡ ጥቅምት 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብን ሰላም እና የሀገሪቱን ቀጣይነት እስካረጋገጠ ድረስ ለውጪ ጫና ሸብረክ ሳይባል በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ተጠያቂነት የሰፈነበት ማንኛውም አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር፣ በማንኛውም የአማራ ክልል እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ ወርቁ ካሰው ተናግረዋል።
ሉዓላዊ ግዛት፣ መንግሥት እና ሕዝብ ያላቸው ሀገራት በመርህ ደረጃ ለሰው ልጆች ምቹ እና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር በሚል በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ አደረጃጀት ፈጥረዋል።
ይሁን እንጂ በኢኮኖሚ የፈረጠሙ ሀገራት ለመልካም ዓላማ የተፈጠረውን አደረጃጀት እንደ ሽፋን በመጠቀም ከተቋቋሙበት ቻርተር፣ ሕግ እና ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ ድብቅ አጀንዳቸውን ሲያስፈጽሙ ተስተውሏል። በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተረጋገጡ ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ፣ በሰላም የመንቀሳቀስ፣ ሠርቶ የመብላት፣ በሕይወት የመኖር፣ ከስጋት ነጻ በሆነ መንገድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የመፈጸም መብቶች ሲገደቡ ቤንዚን ከመጨመር የዘለለ ሚና እንዳልነበራቸው ከፈረሱ ሀገራት ታሪክ መረዳት ይቻላል ባይ ናቸው አቶ ወርቁ ።
እነዚህ ሀገራት ዝቅተኛ ምጣኔ ሀብት ባላቸው ሀገራት ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችላቸውን መረጃ በመሰነድ በፈለጉት አቅጣጫ በማይመሩት ላይ ማዕቀብ መጣል፣ በባለስልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ ማድረግ እና የምንዛሬ ክልከላን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን እስከማሳለፍ ይደርሳሉ። እርዳታ ለመስጠት ወይንም ብድር ለማቅረብም ጥቅማቸውን የሚያስከብር ቅድመ ሁኔታ ያመቻቻሉ።
ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ በገጠማት ፈተናም ተስተውሏል። ሕዝቡ በሕይወት የመኖር፣ እንደ ሕዝብ አብሮ የመቆየትና ሀገርን የማስቀጠል ትግል ላይ እንደሆነ ይታወቃል። አሸባሪው የትህነግ ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት እንደ ሀገር በግለሰብ ደረጃ የመኖር ሕልውና አደጋ ላይ ወድቋል። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ያላደገ፣ በልቶ ማደር ያልቻለ ሕዝብ የበዛባት፣ የኑሮ ውድነት ጣሪያ የደረሰባት፣ የሰላም እጦቱም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ በየመንደሩ ሕገወጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ ፈተናዋ የበዛባት ሀገር ሆናለች።
ሰው ከመኖሪያ ቤቱ እየተፈናቀለ ሠርቶ መብላትም ሆነ ሀብት አፍርቶ ቤተሰቡን መምራት አልቻለም። ለረጅም ጊዜ ያፈራውን ሀብቱን በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ተዘርፏል፣ ወድሟልም። በረጅም ጊዜ የተገነቡ እንደ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎች የመሳሰሉ መሠረታዊ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ስልታዊ በሆነ መንገድ እየወደሙ ነው። በዚህም የዜጎች የመማር፣ የጤና አገልግሎት የማግኘት እና በሕይወት የመኖር መብት ተጥሷል።
ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ሕዝብ፣ ባህል እና ሀገር እንዳይቀጥል ስውር አጀንዳ ያላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተራድኦ ድርጅቶች እና ሀገራት ኢትዮጵያ ለገጠማት ፈተና መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጥቅማቸውን በሚያስከብር መልኩ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ለዚህም አንድን ክልል ብቻ እንደተበደለ አስመስለው የፌዴራል መንግሥትን በተደጋጋሚ ሲተቹ ይስተዋላል። ትግራይ ክልል ተከሰተ ከሚባከው ችግር በበለጠ አማራ፣ አፋር እና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን ጨንሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋለ ነው። እነዚህን ችግሮች ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዝምታ ማለፋቸው ተግባራቸው የሕዝብን ጥቅም ያላማከለ የመሆኑ ማሳያ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕር እና በማናቸውም የአማራ ክልልና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው ወርቁ ካሰው እንዳሉት ጩኸት የበረታው የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን አሸባሪው ትህነግ የአጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ስለሆነ ብቻ ነው።
አቶ ወርቁ የሀያላኑን ማስፈራሪያ የተቀበሉ ሀገራት መጨረሻቸው መፍረስ እንደሆነ አንስተዋል፤ አልቀበልም ብለው በአቋማቸው የጸኑ ደግሞ ክብራቸውን አስጠብቀው ከኀያላን ተርታ እስከመሰለፍ ደርሰዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዘላቂ ጥቅሟ አንጻር የራሷን አማራጭ በመጠቀም የተከፈተባትን ዘመቻ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይጠበቅባታል። ለዚህም በግዛቷ የተፈጠረውን ችግር በሚገባ የተገነዘበና ነገን ታሳቢ ያደረገ የሥራ መሪ እንዲሁም ለችግሩ ተራማጅ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። መንግሥት የሕዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶችን የማስቀጠል፣ በሰላም ተኝቶ የመነሳት፣ ሠርቶ የመለወጥ ሁኔታን የማመቻቸት የቤት ሥራ ይጠብቃል።
አቶ ወርቁ እንደነገሩን መንግሥት ሕልውናውን አስጠብቆ ራሱ ባወጣቸው ሕጎች እና ባደራጃቸው ተቋማት የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት የማረጋገጥ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት አለበት።
የሕዝቡን ሠርቶ የመብላት እና የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ቀድሞ የሕልውና ዘመቻውን ማጠናቀቅ ይገባል። ለዚህም አሸባሪውን ቡድን ከነአስተሳሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ይገባል። ዘመቻው ተጠናቀቀ የሚባለው ግን ጠላትን በውጊያ በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ማኅበራዊ ችግር ማስተካከል እና የውጪ ግንኙነቱን መስመር ማስያዝ ሲቻል ብቻ ነው። ለዚህም የሀገሪቱን ህልውና እና የሕዝቧን ዘላቂ ጥቅም እስካረጋገጠ ድረስ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ተጠያቂነት የሰፈነበት ማንኛውም አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ መወሰድ አለበት።
ማኅበረሰቡን በተገቢ እና በተደራጀ አግባብ ማስተባበር፣ ሀገር በቀል ሀብት እና እውቀትን በአግባቡ ተጠቅሞ መልማት አንዱ አማራጭ መሆኑን ነው ያነሱት።
ለፐብሊክ ዲፕሎማሲው ልዩ ትኩረት በመስጠት በመረጃ ስህተት የሚፈጠር ክፍተት ካለ የማጥራት፣ ሆን ተብሎ ተጽዕኖ ለማድረስ የሚሠሩትን ደግሞ ቁርጥ ባለ አቋም ማስረዳት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ፈታኙን ወቅት ለማለፍ ሕዝቡ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መደራጀት እና መተባበር እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ከስሜት ነጻ ሆነው በተናበበ መልኩ የሀገርን ጥቅም እና የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ማከናወን አለባቸው ብለዋል።
የሕልውና ዘመቻው ሲጠናቀቅ ፖለቲካው ይስተካከላል፤ የውስጥ አጀንዳዎች መስመር ይይዛሉ፤ በየአካባቢው እያቆጠቆጡ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም እድል ይሰጣል። ሕዝቡን አደራጅቶ በልማት ለማስተሳሰርም በር እንደሚከፍት አስረድተዋል ።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየዲጂታል ዲፕሎማሲውን ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ጋር በጣምራ ለማስኬድ ትኩረት ተሰጥቷል።
Next articleበሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በኢትዮጵያ መር በአፍሪካ ድጋፍ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።