የተሰበረ የልጅነት ቅስም!

351

ጥቅምት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ቀኑ መስከረም 27/2014 ዓ.ም ነው፤ ቦታው ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፤ በዕለቱ ከሁለት ወራት በላይ አካባቢውን ወርረው የቆዩት የአሸባሪው ትህነግ ቡድን አባላት የሦስት ሴቶችን ቅስም ክፉኛ ሰበሩት፡፡ ከሦስቱ ልጆች አንዷ ጡት ያልጣለ ሕፃን ከጀርባዋ ላይ አንቀልባ ውስጥ ሆኖ ክፉኛ ያለቅሳል፡፡ አረመኔዎቹ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ለዚህ ሕጻን እና “ከልጄ በፊት እኔ ልሙት” እያሉ በልመና ለሚያነቡት ደካማ እናት እንኳን ቅንጣት ርህራሄ አልነበራቸውም፡፡

አንደኛዋ ልጃገረድ ጊዜ ፈቅዶ ቢሆን ኖሮ በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተናን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበረች፡፡ ሌላኛዋ ደግሞ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ከዚህ በላይ ስለቤት እመቤቷም ሆነ ስለልጃገረዶቹ ማንነት መናገር ለጊዜው አላስፈለገንም፡፡ የልጅነት ቅስማቸውን የሰበረውን እኩይ ድርጊት ግን ከልጆቹ አንደበት እየሰማን እንደዚህ ከትበነዋል፡፡

የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ወደ አካባቢው ዘልቀው ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ዜጎች የእረፍት እንቅልፍ የላቸውም፡፡ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ዱቄት፣ የበሰለ ምግብ፣ መሳሪያ እና ቁሳቁስ በየሰፈሩ እየዞሩ ሲሰበስቡ የባጁት የሽብር ቡድኑ አባላት በዕለቱ ወደ ልጃገረዶቹ ቀዬ ሲያቀኑ ነዋሪዎቹ የተለየ ነገር ይኖራል ብለው አላሰቡም ነበር፡፡ ነገር ግን የሆነው ሁሉ ከሦስቱ ልጆች አዕምሮ ውስጥ ያልጠፋ፣ አንገታቸውን ያስደፋ፣ የልጅነት ሕልማቸውን በአጭሩ የቀጨ እና አሁንም ድረስ ራሳቸውን እንደጥፋተኛ ቆጥረው የሚያነቡበት ሆኖ አለፈ፡፡

በቡድን በቡድን ሆነው የገቡት የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት በየሰፈሩ እየዞሩ የተለመደ ሥርቆት እና ዘረፋቸውን ከምጣድ ላይ የወጣ እንጀራ ሳይቀር ይሰበስባሉ፤ ይህ ለአካባቢው ነዋሪዎች ከወራት በኋላ የለመዱት ጉዳይ ሆኗል፡፡

“ብር አምጡ እና የተደበቁ ወጣቶችን አጋልጡ” እያሉ ሕዝቡን እረፍት የነሱት እነዚህ እፉኝቶች ከሦስቱ ልጃገረዶች ላይ ግን በተለየ ሁኔታ በረቱባቸው፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት ብር አምጭ ሲሏት እንደሌላት ስትናገር በጥፊ እና በክላሽ ሰደፍ መትተው መሬት ላይ የጣሏት ልጅ ከአንቀልባ ላይ ተንጠልጥሎ ለሚያለቅሰው ሕጻን ልጇ እና መሬት እየቧጠጡ ለሚጮሁት እናቷ እንኳን ርህራሄ ማድረግን አልፈለጉም፡፡ በድብደባ ብዛት በኋላ መሬት ላይ የወደቀችው ልጅ ሰማይ እና ምድር ዞሮባታልና የነቃችው ከብዙ ቆይታ በኋላ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ልጇ እና እኗቷ እያለቀሱ የሰፈር ሰዎች በተሰባሰቡበት የደፈሩት ማፈሪያዎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል፡፡

የድርጊቱ ሕመም እና የልብ ስብራቱ ግን ሁሌም ከእኔ ጋር ይኖራል የምትለው እህት በፍትሕ አደባባይ ዋጋቸውን የሚያገኙበት ጊዜ ግን ሩቅ ሊሆን አይገባም ብላለች፡፡

ሌላኛዋ ልጃገረድ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ከወራት ጀምሮ እረፍት ባጣው ቀያቸው የሽብር ቡድኑን የቀን ከቀን ግልምጫ እና ማስፈራራትን ተቋቁመው አካባቢያቸውን ካለቀቁት መካከል አንዷ እርሷ ነች፡፡ “ሞሰብ ገልብጦ እንጀራ መውሰድ፣ ከማጀት ዱቄት እና ቡሆ ተሸክሞ መውጣት” የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት የተለመደ ተግባር ነው የምትለው ይህች ልጃገረድ በዚህ ልክ የወረደ እና ከሰዋዊነት ያፈነገጠ ድርጊት ይፈጽማሉ ብላ አስባ እንደማታውቅ ተናገራለች፡፡

ተሰባስበው ወደ ቤታቸው የገቡት የትህነግ ሽብር ቡድን አባላት እንደተለመደው የሚፈልጉትን ከዘረፉ በኋላ ግን ሁለቱ ወደ ኋላ ቀርተው ያንገላቷት ጀመሩ፡፡ በተደጋጋሚ ለመጮኽ ያደረገችው ሙከራ ግን ራሷን ከማድከም ውጭ መፍትሄ ማምጣ አልቻለም፡፡ “አንዱ ፊት ለፊቴ ቆሞ ከአንገቴ ላይ ጩቤ እና ከደረቴ ላይ መሳሪያ ደገነብኝ” ትላለች ከዐይኗ የሚፈሰውን የእምባ ዘለላ ለመቆጣጠር እየተሳናት፡፡ ሌላኛው አረመኔአዊ ግብሩን ነገን በሩቅ ከምታለምው ልጃገረድ ላይ ፈጸመ፡፡

ይህ አስነዋሪ ድርጊት ጉዳቱ የደረሰባትን ብቻ ሳይሆን አድማጮቹንም የከፋ ሃዘን ውስጥ ከትቷል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን ከአስነዋሪ ድርጊቱ ሳያንሰው ከአዕምሮዋ የማይጠፋ ክፉ ቃል ጭምር ይወረውር ነበር አለች፡፡ እኛ ትንሽ ስለተማርን የደረሰብንን በደል በከፊልም ቢሆን ወደ አደባባይ አወጣነው የምትለው ተጎጅዋ ጉዳታቸውን ጉዳት አድርገው እና በውስጣቸው እያለቀሱ በየቤታቸው ያሉትን ግን ቤት ይቁጠራቸው ብላናለች፡፡

ሌላኛዋ ተጎጂ ሀገር ሰላም ሆኖ ቢሆን ኖሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበረች፤ “በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” የምትለው ልጃገረድ አሁን ግን ለፈተና የሚሆን የሥነ ልቦና ዝግጅት እንኳ ያለኝ አይመስልም ትላለች፡፡ በዕለቱ የደረሰባትን በደል ስትናገርም የመንታ መንታ ሆኖ የሚፈሰውን እምባዋን እና ጉሮሮዋን የሚተናነቃትን ሳጓን መቋቋም ተስኗት ነበር፡፡ ሕልም ነበራት፤ ተምራ እና ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳ ሳይኖራቸው አኑረው የሚያስተምሯትን ቤተሰቦቿን ውለታ መክፈል፡፡ ሦስት ሆነው በመፈራረቅ ሰውነቷ ላይ የወደቁት ባለጌዎች ያንን ትልቅ ሕልም ከንቱ፤ ያንን ሩቅ አሳቢ ቅስም በለጋነቱ ሰበሩት፡፡ “ሦስት ሆነው ወደ ቤት መጡ” የምትለው ተጎጂዋ በመጀመሪያ የጠየቋት ገንዘብ ቢሆንም እንደሌላት ስትነግራቸው ግን ከሰውነት ወርደው መሬት ላይ ጣሏት፡፡ የሚፈልጉትን በቀል ያደረሱት የሽብር ቡድኑ አባላት በደም ለጨቀየው ሰውነቷ እንኳን እዝነትን ሳያሳዩ ጥለዋት ወደመጡበት ሄዱ፡፡

“ሕልም ከመሰለው ክፉ ሰመመን ስነቃ ግን የሕይዎት ጉዞዬ እንደተጠናቀቀ ሁሉ ነገሮች ጨለማ ሆነውብኝ ነበር” የምትለው ተጎጂዋ ነገ አጥፊዎች በፍትሕ አደባባይ ፊት የሚቆሙበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑ መጽናኛ ነው ትላለች፡፡

ተጎጂዎቹ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ወደ ፍላቂት መጥተዋል፡፡ አስፈላጊው የሕክምና ክትትልም በቅርብ ርቀት እየተደረገላቸው ነው፡፡ አንድ ጽኑ ፍላጎት ግን አላቸው “የሽብር ቡድኑ አባላት ተጨማሪ ጉዳት እና በደል ሳያደርሱ ከአካባቢያቸው እንዲጸዱ”ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝቡ በመከራ ውስጥ ነው የሚሉት እነዚህ ተጎጂዎች መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ወስዶ ወገኖቻቸውን እንዲታደግ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከመቄት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ መሬት ሊያወርደው ይገባል” መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ በመስኖ የለማ የስንዴ ማሳን እየጎበኙ ነው።