“የተከሰተውን የዋጋ ንረትም ሆነ የኢኮኖሚ ግሽበት ለመቆጣጠር ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሊያግዝ ይገባል” የኢኮኖሚክስ መምህር

167
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ባለው የህልውና ዘመቻ የሚታየው የኢኮኖሚ ግሽበትና የዋጋ ንረት አሸባሪው ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በሀገሪቷ የሠራው የኢኮኖሚ አሻጥር ውጤት መሆኑን በራያ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና ኢኮኖሚክስ መምህር ዳሞት አለኸኝ ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ግሽበትንም ሆነ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መንግሥት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ መቋጨትና እንደህልውና ዘመቻው ሁሉ አስቸኳይ የኢኮኖሚ ሽግግር ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የህልውና ጦርነት ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እያስተናገደች እንደሆነ አስገንዝበዋል። የፋይናንስና ኢኮኖሚክስ መምህሩ አሁን ላይ የኑሮ ውድነቱ ማኅበረሰቡን ችግር ውስጥ ከቷል ብለዋል።
ይህም ባለፋት 27 ዓመታት አሸባሪው ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ይከተለው በነበረው ፖሊሲ ውስጥ ራሱና ያሠማራቸው ቡድኖች የሚዘርፋበትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አውስተዋል።
ዛሬ ላይ ከጦርነቱ ባሻገር ለደረሰው የኢኮኖሚ ግሽበትም ሆነ የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያት ይኸው ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የሰራው የኢኮኖሚ አሻጥር ድምር ውጤት መሆኑን ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህር ዳሞት አለኸኝ አብራርተዋል።
ትህነግ በስልጣን ዘመኑ የሀገሪቱን ሀብት ንብረት ከመዝረፍ ባሻገር በተለየ ሁኔታ ጠላቴ ብሎ የፈረጀውን የአማራ ሕዝብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሀብት ንብረት አፍርቶ እንዳይኖር ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል።
አሁን ላይ ትህነግ ወረራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሀብት በመዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ በማውደም የኢኮኖሚ ኪሳራ ማድረሱን የተናገሩት መምህሩ እንዲህ አይነት ክስተቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እንደ ህልውና ዘመቻው ኢኮኖሚውንም ለማረጋጋት በዘመቻ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
አሁን ባለው የህልውና ዘመቻ የሚታየውን የዋጋ ንረትም ሆነ የኢኮኖሚ ግሽበት ለመቆጣጠር በአዲስ የተመሠረው መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መገንባት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የተከሰተውን የዋጋ ንረትም ሆነ የኢኮኖሚ ግሽበት ለመቆጣጠር መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ተግባር ባለመሆኑ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሊያግዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:–ዘመኑ ይርጋ– ከፍኖተ ሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleʺበአዛኝቱ ምሎ ምኒልክ ሲመካ፣ ፈረሱ ዓባዳኘው ደስ ብሎት አሽካካ”
Next article“መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ መሬት ሊያወርደው ይገባል” መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ