ʺበአዛኝቱ ምሎ ምኒልክ ሲመካ፣ ፈረሱ ዓባዳኘው ደስ ብሎት አሽካካ”

465

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዳዊት የልጅ ልጅ፣ የጠቢቡ ሰሎሞን ልጅ፣ የንግሥተ አዜብ ልጅ፣ በኢየሩሳሌምም፣ በኢትዮጵያም የነገሥታት ልጅ ንጉሥ እየተባለ የሚጠራ፡፡ ከነገሥታት ወገን የሆነ፡፡ በኢየሩሳሌም በሰሎሞን ቤተመንግሥት በአማረ አልጋ፣ በድንቅ ጥበብ በታነጸ መኝታ ቤት ውስጥ ተጸነሰ፡፡ ባመረው አልጋ የተዋወቁትን ንግሥትና ንጉሥ አዳራቸው ተባረከላቸው፡፡ ዝናው ከፍ የሚል ልጅ ተሰጣቸው፡፡ በኢየሩሳሌም በሰሎሞን ቤተመንግሥት የተጸነሰው ደገኛ ልጅ በቃል ኪዳኗ ምድር በኢትዮጵያ ተወለደ፡፡ አቤ ሜሊክ፣ ምኒልክ ተሰኘ፡፡ አበው ለዚህ ስም የተለያየ ትርጓሜ ሰጡት፡፡ ከትርጓሜዎች ሁሉ ምን ይልክ ይሆን እግዚአብሔር የሚለው ለስሙ የተገባ ነው ይቀርበዋልም ይላሉ፡፡

ከነገሥታትና ከካሕናቱ ወገን የተገኘው ብላቴናው ምኒልክ የአባቱን የሰሎሞንን ጥበብ ተማረ፡፡ ጥበብን ከአባቱ ተምሮ በጠቢቧ እናቱ እቅፍ ውስጥ አድጎ ሀገር እናት ናትና የእናቱን ሀገር ምርጦ በእናቱ በአዜብ ዙፋን ላይ ተቀመጠ፡፡ በምድርም ትልቁ ስጦታ ተሰጠው፡፡ ታቦተ ጽዮንንም በእናቱ ሀገር አስቀመጠ፡፡

ዘመን ዘመንን እየተካ መጣ፡፡ በዚያ ዘመን ገናና የነበረውን ስም ይዘው ሌላ ንጉሥ በኢትዮጵያ መጡ፡፡ የቀደመው ምኒልክ ከተቀመጠበት ዙፋን ላይ ሊቀመጡ፡፡ የንጉሥ ሳሕለ ስላሴ የልጅ ልጅ፣ የኃይለ መለኮትና የእጅጋየሁ ልጅ፣ በአንጎለላ ተወለዱ፡፡ በጥበብ የተወለደው ልጅ ያስደነቃቸው አያቱ ʺ ምን ይል ሸዋ” ሲሉ ምኒልክ አሏቸው፡፡ አበው ግን ምስጢሩ እንደ ቀደመው ስም ምን ይልክ ይሆን እግዚአብሔር ለሚለው የተገባ ነው ይላሉ ምኒልክ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ፡፡ በጥበብ አደጉ፡፡ ክብራቸው ለዙፋን አስቀድሞ የተመረጠ ነበርና ጊዜው ደርሶ በአስፈሪው ዙፋን ተቀመጡ፡፡

ምኒልክ በነገሡበት በዚያ ዘመን የጥቁሯ ምድር አፍሪካ መከራዋ የበዛ ነበር፡፡ ነጮች በጥቁሮች ላይ ያለ ከልካይ በደል ይፈጽማሉ፣ የግፍ ግፍ ይሰራሉ፣ ጥቁርን በእቃ እየለወጡ ይሸጣሉ፡፡ ደራሽ ያጠው ጥቁር ሁሉ በተወለደበት ሀገር፣ በፈቃድ በተሰጠው ምድር እየተቅበዘበዘ ይኖር ነበር፡፡ የነጮች የግፍ እጅ ረዝሞ አባዳኛው የነገሡባትን፣ ከነብሳቸው አብዝተው የሚወዷትን ሀገር ሊበድል እጁን ዘረጋ፡፡ አባዳኛው ግን በኢትዮጵያ ላይ በግፍ የሚዘረጉ እጆች ይቆረጣሉ፣ ለበረከት የሚዘረጉ እጆች መና ይቀበላሉ እንጂ አይሆንም፣ አይደረግም አሉ፡፡

ʺኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚል እንጂ ኢትዮጵያ ለጠላት እጆቿን ትሰጣለች የሚል ታሪክ ፈጽሞ አልሰፈረባትምና የአባዳኘውን ሀገር የሚደፍር የለም፡፡ በዘመኑ በአውሮፓ ኃያል የነበረው የሮም መንግሥት ኢትዮጵያን ይወር ዘንድ በብዙ ነገር ቋመጠ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋርም ቅርርብ ፈጠረ፡፡ ውልም ተፈራረሙ፡፡ የውጫሌ ውል፡፡ ይህ ውል መዘዝ ይዞ መጣ፡፡ መሰሪው የሮም መንግሥት ኢትዮጵያን በስልት የሚገዛበትን መንገድ አመቻችቶ ኖሮ በመካከል ጥል ፈጠረ፡፡ መዘዘኛዋ አንቀጽ 17 ሁለቱን ሀገራት አፋጠጠች፡፡ በጠላቶቹ ላይ እንዲሰለጥኑ፣ ጠላቶቻቸውንም አሸንፈው ሀገራቸውን እንዲያስከብሩ አሸናፊነትና ፈሪያ እግዚአብሔርነትን የተቸራቸው ታላቁ ንጉሥ ጣልያን ባሰበችው መንገድ ኢትዮጵያ እንደማትስማማ እንቅጩን ተናገሩ፡፡

ʺኢትዮጵያ በኢጣልያ ጥግ ትኖራለች የሚል ነገር እንኳን በውኔ በሕልሜም አላሰብኩት” አሉ፡፡ ለአውሮፓ ነገሥታትም ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ትኖራለች እንጂ በኢጣልያ ጥግ ልትኖር ምንም ውል አላደረኩም እወቁልኝ ሲሉ አሳወቁ፡፡ ጣልያንም ነገሩን እርሷ ባሰበችው መንገድ ለመፍታት ያስችላት ዘንድ ኮንት አንቶሎኒ የተባለውን መልእክተኛዋን ወደ ኢትዮጵያ ላከች፡፡ መልእክተኛው ግን እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ በምኒልክ ቤተመንግሥት እየተመላለሰ ሊያሳምን ሞከረ፣ አባዳኛውና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ በሀገር ላይ ድርድር አይደረግም አሉ፡፡ ተስፋ የቆረጠው መልእክተኛውም ፍቅራችን ፈረሰ ብሎ በነገሥታቱ ፊት በጦርነት እንደሚመጡም ዝቶ ወጣ፡፡

በዚያን ጊዜ የተናደዱት እቴጌ ጣይቱ ʺ የዛሬ ሳምንት አድርገው በዚሕ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣውን እናነሳዋለን፣ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው ከዚህ ያለ አይምሰልህ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው፣ እንጂ ሞት አይባልም፡፡ አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፈከርክበትን በፈቀድህ ጊዜ አድርገው እኛም እዚሁ እንቆይሃልን” ማለታቸውን አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ጽፈዋል፡፡ ኮንት አንቶሎኒ ወደ ሮም ከተመለሰ በኋላ ጣልያን ዶቶር ትራበርሲን የተባለ ሌላ መልእክተኛ ወደ ኢትዮጵያ ላከች፡፡ ነገሩ በፍቅር እንዲፈታ ፍላጎት አለኝም አለች፤ ዳሩ ግን በሮም ኢትዮጵያን የሚያጠቃ ሠራዊት እየተዘጋጀ ነበር፡፡ አባዳኛውም ቢሆኑ ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ በሰላም መስማማት አልተቻለም፡፡ ጦርነቱ የማይቀር ሆነ፡፡ ጣልያን የኢትዮጵያ አውራጃዎች ያዘች፡፡ ምኒልክ አዋጅ አስነገሩ፡፡

ʺእግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከበት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር እረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኃላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ” የአባደኘውን አዋጅ የሰማ የሀገሬው ሰው ትጥቁን አጥብቆ ስንቁን ሰንቆ ወደ ተባለበት ሥፍራ ተመመ፡፡

ሞቶ ሀገርን ለማኖር፣ በጀግንነት ታሪክን ለመዘከር ሲል ሞት ወደ አለበት ሥፍራ ለሠርግ እንደተጠራ ሁሉ በቀረርቶና በፉከራ በታላቅ ሀገር ፍቅር ገመድ ታስሮ ከተተ፡፡ ንጉሡም ለዘመቻ የሚነሱበት ቀን ደረሰ፡፡ ወረሃ ጥቅምት በገባ በሁለተኛው ቀን ነጋሪት አስጎስመው፣ ፈረሳቸውን አስጭነው፣ መኳንንቱን አስከትለው በታላቅ አጀብ ከቤተመንግሥታቸው ለዘመቻ ተነሱ፡፡ ያም ዘመን ልክ በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 2 ቀን 1888ዓ.ም ነበር፡፡
ʺ በአዛኝቱ ምሎ ምኒልክ ሲመካ፣
ፈረሱ ዓባዳኘው ደስ ብሎት አሽካካ” ምኒልክ በማርያም ምለው ተነሱ፡፡ ፈረሳቸው አሽካካ፣ ወደ ድል ተራራው ገሰገሰ፡፡ አቧራው ጨሰ፣ መንገዶች ተናወጡ፣ ጉድ ተባለ፡፡ ከዳር እስከ ዳር የንጉሡን አዋጅ የሰማው የሀገሬው ሰው ሠንደቁን አስቀድሞ፣ በኢትዮጵያ ስም ተማምሎ ገሰገሰ፡፡ የጦርነቱ ገዜም ደረሰ፡፡ በአምባላጌና በመቀሌ የነበረውን ጠላት ድባቅ መትቶ ወደ ዓደዋ አቀና፡፡ በእለተ ሰንበት በዓድዋ አናት ላይ የነጭ አቢዮት ፈራረሰ፣ የኃያላኑ የክፋት ሰንሰለት ተበጣጠሰ፣ ጥቁር ከፍ ብሎ ነገሠ፣ በግፍ የተገዙት ጥቁሮች ደም ተመለሰ፡፡ ዓለም ያልገመተው፣ ያላሰበው ጀብዱ ተፈጽሞ ነበርና ዓለም ደነገጠች፤ እንደምንስ ሆነ አለች፡፡ የጀግንነት ታሪክ በጀግና መሪ እየተመሩ በጀግኖች ተፈጽሟልና፡፡
ለዘመቻ ከመነሳታቸው አስቀድሞ ʺእኛ ግን እንኳን ለእልፍ ለሁለት እልፍ ሰው የኢጣልያ አገር ሰው ሁሉ ቢመጣ የኢጣልያን ጥገኝነት ይቀበላሉ ብለህ አትጠራጠር” ያሉት አባዳኛው በዓድዋ ላይ ቃላቸውን ፈጸሙ፡፡ መመኪያቸውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ፣ በክብር ከተራራው አናት ላይ ሠንደቃቸውን አውለበለቡ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው የታሪክ ጸሐፊውን ቤርክሌይ ጆርጅን ሀሳብ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል ʺሃያ ሺህ ያህል ያሉበት የኢሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እመነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ያለ ጦርነት የለም፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁሩ ዓለም በኢሮፒያዊያን ላይ ሲያምጽና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልእክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡ አሁን የሁሉንም ፍላጎት ዓድዋ ዘጋው፡፡” አዎን ዓድዋ የክፋትን በሮች በሙሉ ዘግቷል፡፡ ዓድዋ ፍትሕን፣ አንድነትን፣ ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ የጸና ኢትዮጵያዊነትን፣ አይደፈሬነትን፣ አሸናፊነትን አምጥቷል፡፡

አባዳኘው በሙሉ ልብ፣ በቆራጥነት፣ በታላቅ ሀገር ፍቅር ዘመቻ የጀመሩባት ቀን ዓድዋን ያስገኘች፣ የአሸናፊነትን ጉዞ የጀመረች፣ የአምባገነኖችን ዘመን የፈጸመች የአፍሪካን ጀንበር ያዘለቀች፣ የሮምን ፀሐይ ያጠለቀች ናት፡፡ ታለቁ መሪ፣ ለታላቅ ድል የተነሱባትን ታላቅ ቀን ልናስባት ወደድን፡፡ ዛሬም ለነጻነት ተነስ፣ በአንድነት ገስግስ፣ በጀግንነት ተመላለስ፡፡ ታሪክ ያከበርዎ ንጉሥ ሆይ ዛሬም ይከበራሉ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleባህሬን ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ሀገራዊ ለውጥ እንደምትደግፍ አስታወቀች።
Next article“የተከሰተውን የዋጋ ንረትም ሆነ የኢኮኖሚ ግሽበት ለመቆጣጠር ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሊያግዝ ይገባል” የኢኮኖሚክስ መምህር