ሁሉም ዲፕሎማት ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በንቃት በመገንዘብ በየተመደበበት ተልዕኮ ለስኬት መትጋት እንደሚገባ አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

146
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሠራተኞች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ተጠሪ ተቋማት የተዘጋጀው ሁለተኛው ዙር ስልጠና መርሃ ግብር መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም ዲፕሎማት ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በንቃት በመገንዘብ በየተመደበበት ተልዕኮ ለስኬት መትጋት ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና በዓለም አቀፋ ደረጃ ያላትን አወንታዊ ገፅታ ለማስፋት ዋናው መስሪያቤት ከማጠናከር ጀምሮ ኤምባሲዎችን እና ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶችን የማደራጀት ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከውስጥም ከውጭም የተደቀነውን ፈተና ለመቀልበስ በትብብር እና በመናበብ የሚራመዱበት ወቅት ነው ብለዋል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ በተጀመረው ስልጠና ተሳታፊ የሆኑ የሁለተኛው ዙር ሰልጣኞች በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሔደ ያለውን ዘርፈ ብዙ የተቋማት ማሻሻያዎች እና አደረጃጀቶችን በማጤን እኔ ለሀገሬም ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ምን ሠራሁ በማለት ራሳቸውን በመጠየቅ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ማሻሻያ እና ክለሳ በማጠናቀቅ የመጨረሻውን ግብዓት እየሰበሰበ መሆኑንም አቶ ደመቀ ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ እና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ በመሆናቸው በሀገራችን ጥቅም ላይ ጥላ እንዳያጠላ የመቀልበስ እና አዎንታዊ መረጃዎችን የማስፋት ሥራም መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሥልጠና ለቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleʺለሠንደቁ ክብር ይሞታሉ፣ በሠንደቁ ጥላ ሥር ይኖራሉ”
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም ዕትም