
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሠንደቁ አምላክ የተገዘተ እጁን ለጥል አያነሳም፣ ለበቀል አይነሳም፣ የሠንደቁን ግርማ ጥሶ፣ ክብሩን አርክሶ መሄድ መራመድ ነውር ነው፡፡ ሠንደቅ ዓላማው ከክብር ክብር፣ ከፍቅርም የላቀ ፍቅር፣ ከምስጢርም የላቀ ምስጢር ነው፡፡ ስለ ሠንደቁ ክብር መዝመት፣ መሞት፣ ሕይወትን መስጠት፣ ሠንደቁን አስቀድሞ ለድል መገስገስ፣ በሠንደቁ ግርጌ በድል መመላለስ፡፡ ሠንደቁ ሲነሳ አንገቱን ለሥለት፣ ግንባሩን ለጥይት፣ ደረቱን ለጦር፣ እግሩን ለጠጠር ይሰጣል፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ አስቀድሞ ዘምቶ ያፈረ የለም፡፡ ከሠንደቁ ጋር ድል፣ መልካም እድል፣ አሸናፊነት፣ አስፈሪነት፣ አንድነት፣ ጀግንነት፣ አይበገሬነት አለ፡፡ እንደ እሳት ይናደፋል፣ እንደ መብረቅ ይወነጫፋል፣ እንደ ሰይፍ ይቀስፋል፣ ኀይል እና ምስጢር በላዩ ላይ አርፎበታልና፡፡ ከሠንደቆች ሁሉ የላቀ፣ ከረቀቁት ሁሉ የረቀቀ፣ ከደመቁት ሁሉ የደመቀ፣ በምድር ሊያጠፉት ሲመኙ በሰማይ የሚያዩት፣ ከጨለማ ግርጌ ሊጥሉት ሲታትሩ ከብርሃን ተራራ ላይ በአሻገር የሚመለከቱት፣ የተጨቆኑት በአሻገር እያዩት የሚከተሉት፣ ወደ ተሰቀለበት ዘላለማዊ ተራራ የሚጎርፉለት፣ የሚጽናኑበት፣ የሚመኩበት፣ ከጨለማ የሚወጡበት፣ ጠላትን የሚያሸንፉበት፣ በጥላው ሥር የሚሰባሰቡበት፣ ድንቅ ሥጦታ፣ አስፈሪ መከታ፣ በግጥሚያዎች ሁሉ የማይረታ ነው፡፡
የኖህ የተስፋ ምልክት፣ የተቀደሰችው ሀገር መጎናጸፊያ፣ የተስፋዋ ምድር ማመላከቻ እያሉ ይጠሩታል፡፡ከነብሳቸው አስበልጠው ይወዱታል፣ ሠንደቁ ሲነሳ በፍቅር ያለቅሳሉ፣ በአንድነት ይዘምራሉ፣ በአንድነት ይዘምታሉ፣ በአንድነት ያሸንፋሉ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በተውለበለበበት ሁሉ ደስታ አለ፣ ማሸነፍ አለ፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ የጨለማውን ዘመን አስቀርቷል፣ የግፈኞችን አንገት አስደፍቷል፣ የተበደሉትን አንገት አቃንቷል፣ የፍትሕን ዘመን አምጥቷል፣ የኃያላኑን ዙፋን አንኮታኩቷል፣ ሥለ ሠንደቁ ክብር ደም እንደ ቦይ ውኃ ፈስሷል፣ አጥንት ተከስክሷል፡፡ የኢትዮጵያ መለያ ምልክት፣ የኢትዮጵያዊያን በረከት፣ በምድርም በሰማይም ይወለበለባል፣ ኢትዮጵያዊያን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ከጦራቸው ጫፍ እያሰሩ፣ ከፈረሳቸው ግንባር እየሰቀሉ፣ በበረሃ እየተጓዙ ሀገር አቀንተዋል፣ ታሪክ ሰርተዋል፣ ስልጣኔን አስፋፍተዋል፡፡ በሠንደቁ እየተመሩ በደለኞቹን አሸንፈዋል፣ በሠንደቁ እየተመሩ የማያረጅ ታሪክ ጽፈዋል፣ የማይረሳ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡
የነጭ ግፈኝነት በነበረበት፣ ጥቁር እንደ ሸቀጥ ገበያ ላይ በዋለበት፣ እንደ ሰው ባልተቆጠረበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ሠንደቃቸውን ከፍ አድርገው፣ በሚወዱትና በሚወዳቸው አምላካቸው እየተመኩ ጫፋቸውን ሳያስነኩ ኖረዋል፡፡ የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን ሀገር ለማጥቃት፣ ኢትዮጵያዊያንንም ለመግፋት ጠላቶች በየዘመናቱ ክንዳቸውን አንስተዋል፣ ሊወጓት ጦራቸውን አዝምተዋል፣ ባሕር ቆርጠው፣ የብስ አቋርጠው መጥተዋል፤ ዳሩ አንዳቸውም ያሰቡትን አላደረጉም፡፡
እርሷን ማሸነፍ የተቻለው ጠላት አልተገኘም፡፡ አይገኝምም፡፡ ፊደል የቀረጸች፣ ሐውልት ያነጸች፣ ቤተ መቅደስ በጥበብ የሠራች፣ በጦርነት ያልተሸነፈች ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በተለይም በቀደመው ዘመን በሠንደቁ አምላክ የመጨረሻው ግዝት ነበር፣ በሠንደቁ አምላክ የተገዘተ ወንዙን አይሻገርም፣ ለግድያ ያዘጋጀውን ምላጭ አይስብም፣ ለመማታት የጨበጠውን በትር አይሰነዝርም፣ በሠንደቁ አምላክ ሲባል ጥሉን ይተዋል፣ ከቁጣው ይበርዳል፡፡
የሠንደቁ ስም ተጠርቶ ክፉ የሚያደርግ ካለ ከማኅበር ይነሳል፣ የማይጣሰውን ጥሷል፣ የማይሻረውን ሽሯልና ከሁሉም ነገር ይገለላል፡፡ በሠንደቁ አምላክ የሚለው ቃላቸው የማይሻር፣ የማይደፈር ሕጋቸው ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሕግ አክባሪዎች፣ በሕግና በሥርዓት ኗሪዎች ናቸውና እንኳን በሠንደቃቸው በንጉሳቸው ስም ከተገዘቱ ክፉ አያደርጉም፣ ለበቀል አይነሱም፡፡ ንጉሡን ያከብራሉ፣ በሕግ ለሕግ ይገዛሉ፡፡ ሕግ አክባሪዎች ናቸውና ፈጣሪ ይወዳቸዋል፣ ይጠብቃቸዋል፣ አሸናፊነትን ይሰጣቸዋል፡፡
ሠንደቁን አስቀድመው ይዘምታሉ፣ ስለ ሠንደቁ ክብር እኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በልባቸው የታተመውን፣ በደማቸው የጸናውን፣ በአጥንታቸው የከበረውን፣ በአንድነታቸው ከፍ ያለውን ሠንደቅ ቀን ሳይመርጡ ያውለበልቡታል፣ ይመኩበታል፡፡ ከቀናት አንድ ቀን መርጠው ደግሞ ቀኑን በስሙ ሰይመው ያከብሩታል፡፡ ክብራቸውና መመኪያቸው ነውና፡፡
የቀደሙት አባቶች የተቀደሰችውን ምድር በጫማ መርገጥ ይፈራሉና በባዶ እግራቸው ይራመዳሉ፣ እርሷን ችለን በጫማ አንረግጥም ይላሉ፡፡ ታላቋን እና የተቀደሰችውን ምድር ያከብሯታል፣ ይከበሩባታል፡፡
አክብረው ስለ ጠበቋት አላስነኳትም፣ የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ ስለሚጠብቁ ፈጣሪ አልተዋትም፡፡ አንተም አክብራት እናትህ ናት፣ አንተም አክብራት መመኪያህ ናት፣ አንተም አክብራት መከበሪያህ ናት፣ አንተም አክብራት መቅደሚያህ ናት፣ አንተም አክብራት የፍትሕ መንገድ ናት፣ አንተም አክብራት የአሸናፊነትህ በትር ናት፣ አንተም አክብራት ጌጥህ ናት፣ አንተም አክብራት በክብር የምታደርጋት አክሊልህ ናት፣ በኩራት የምትቀመጥባት ዙፋንህ ናት፣ ዓለም የምታይባት ማዕረግህና ደስታህ ናት፣ ዘርህን የምትተካባት አጊጠህ የምትኖርባት ትዳርህና ቤትህ ናት፡፡
ሠንደቁ ለኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚለብሱት የማያረጅ ልብሳቸው፣ የሚያጠልቁት ዘላለማዊ ጌጣቸው፣ ከድል ተራራ ላይ የሚያደርሳቸው የጋራ መንገዳቸው፣ ጠላት የሚያሸንፍ ሰይፋቸው፣ ጠላት የሚያስደነግጥ ግርማቸው ነው፡፡ በሠንደቃቸው ለመጣ ወዮለት ክንዳቸውን ይቀምሳል፣ አፈር ይልሳል፡፡
የሠንደቃቸውን ክብር የሚነካውን አይምሩትም፣ አይታገሱትም፣ በደማቸው ቀለሙን ያደምቁታል፣ መስቀያ መሰሶውን ያጸኑታል፡፡ ሠንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያዊያን ከምንም በላይ ነው፡፡ ዛሬም ለሠንደቁ ክብር ተነስ፣ ሠንደቁን አስቀድመህ ገስግስ፣ ሠንደቁን ከጠላትህ መቃብር አናት ላይ ከፍ አድርገህ ስቀለው፣ እንዲታይ አድርገህ አውለብልበው፡፡ ሠንደቁ በምድርም በሰማይም በክብር የኖረ፣ ከምንም ነገር የከበረ መሆኑን ንገረው፡፡ ሠንደቃችን ጌጣችን፣ ሠንደቃችን መመኪያችን፣ ሠንደቃችን ተስፋችን ነው በለው፡፡ ተስፋ ደግሞ በጠላት አይነካም፣ በጥቅም አይለካም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለሠንደቁ ክብር ይሞታሉ፣ በሠንደቁ ጥላ ሥር ይኖራሉ፡፡ በሠንደቁ ፍቅር ይተሳሰራሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር፣ ኢትዮጵያዊነት ምስጢር ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ቅዱስ መንፈስ፣ ኢትዮጵያዊነት የሚያበራ የክብር ልብስ ነውና፡፡ አክብረህ ልበሰው፣ አኖረህ ለልጅ ልጅህ አውርሰው፤ የፍቅሩን በረከት ለዓለም አዳርሰው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ