
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስቴር ሥራቸውን የተረከቡትና ከሚኒስቴሩ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ትውውቅ ያደረጉት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የተጀመሩ መልካም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ችግር መልክ ብዙ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ” ሕዝቡ ከአዲሱ መንግሥት ብዙ ይጠብቃል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል ማስከተላቸውን አስታውሰው “ኢትዮጵያውያን በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል” ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት መከበር ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድነቱን በተግባር እንደሚያሳይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁማ ጸንታ የቀጠለችው ኢትዮጵያውያን ለሰላም ባላቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኀይሎች የሚፈጥሩትን ችግር ሁሉ ተቋቁማ ሀገሪቷ አሁንም ጠንካራ ሆና መቀጠል የቻለችው በሕዝቡ የሰላም ፍላጎት ነው” ብለዋል።
“ሕዝቡ ይህን የሰላም ፍላጎት አጠናክሮ መቀጠል አለበት” ያሉት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ፤ ሰላም ሁሉንም ማሸነፍ የሚችል ትልቅ ኀይል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዜጎች ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ግልጽ አደጋ የደቀኑ ኀይሎችን መመከት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የጸጥታ ኀይሉና ሕዝቡ ያላቸው ቅንጅት ይበልጥ እንዲጎለብት በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m