
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓውያን አዕምሮ ነጭን ማሸነፍ አይቻልም በተባለበት ዘመን አሸናፊ መኾን የቻለች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
በ1888 ዓ.ም አፍሪካን ጠቅልሎ ለመውረር እቅድ የያዙት አውሮፓዊያን የወረራውን ፍፃሜ በኢትዮጵያ ላይ ለማድረግ ተነስተው ነበር፡፡ ዳሩ ግን የዘመኑን ድንቅ መሳሪያ የታጠቅ የጣሊያን ጦር በሰሜን አቅጣጫ ቢመጣም በጥበበኛው ሰው የተመራው ኢትዮጵያዊ ጦር ታሪክ በደማቁ ቀለም የመዘገበውን ድል በአድዋ ተራሮች ሥር ፍጽሟል፡፡
በዚህ የአፍሪካዊያን ድል በሆነው የአድዋ ድል እልፍ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በወኔ ታላላቅ ጀብድ ፈጽመዋል፡፡
የወቅቱ ኀያላንና የዓለም ገዥ የነበሩት አውሮፓውያን ደግሞ መሸነፍ እንደሚችሉ በአደባባይ ያረጋገጠ ድል ነበር-የዓድዋው ጦርነት።
የዓድዋ ድል የተገኘውም ከጫፍ እስከ ጫፍ ክተት የተባለው ሕዝብ የንጉስ ምኒልክ ጥሪ በመቀበል በአንድነት መቆም በመቻሉ ነው፡፡ እምየ ምኒልክ የአንድነት፣ የሩህሩህነት፣ የጀግንነት፣ የስልጣኔ፣ የእውነተኛነት እና የፍትሕ ተምሳሌት ተደርገው የመታየታቸው ምክንያትም ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የነበራቸው ሁለንተናዊ ክብር ነው።
በዚያን ዘመን ኢትዮጵያዊያን የምኒልክን ጥሪ በመቀበል ከአራቱም ማዕዘን ወረኢሉ በመክተት የጸና አንድነታቸውን አሳይተዋል። በአንድነት በመቆማቸውም ኃያላኑን አንበርክከዋል።
የካራማራ ድል ሲታወስም ወቅቱ ልክ እንደ ዛሬው ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቿ ሊያፈርሷት 24 ሰዓት የሚጥሩበት ነበር። ኢትዮጵያ በእጅጉ የተፈተነችበት ያ ጊዜ ልክ እንደ አድዋው የጣልያን ወረራ ሁሉ በሕዝባዊ አንድነት ካልሆነ በስተቀር ሊመከት የማይችል መሆኑን የወቅቱ መሪዎች ጠንቅቀው ተረድተውታል።
የሶማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ “ታላቋ ሶማሊያን” እመሰርታለሁ በሚል ቅዠት ኢትዮጵያን በመውረሩ ሕዝቡ ለሀገሩ ዳር ድንበር ዘብ እንዲቆም መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ሚያዝያ 4/1969 ዓ.ም በቴሌቭዥን መስኮት ቀርበው ጥሪ አስተላለፉ።
“… ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች። … ለብዙ ሺህ ዓመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት! የኢትዮጵያ ሕዝብ! ክብርህንና ነፃነትክን ለመድፈር ሀገርህን ለመቁረስ የተጀመረው ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!” የሚል ነበር ጥሪው።
ከዚህ ጥሪ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ገንፍሎ ተነስቶ በ3 ወር ግዜ ውስጥ ታጠቅ ተብሎ በተሰየመው ማሰልጠኛ ቦታ ሰልጥኖ በመፋለም ነው በካራ ማራ ተራሮች ለደማቅ ድል የበቃው።
ለዛም ነበር ከምሁር እስከ አርሶ አደር ሀገርን የማስቀደም የህልውና ዘመቻ የተካሔደው።
እልፍ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን በክብር ለእናት ሀገራቸው ቢሠውም ድል ግን ከእውነተኛዎቹና ከጀግኖቹ ጋር መሆንን ነበር የመረጠችው። ግዙፉ የዚያድ ባሬ ጦርም በተደራጀው የዘመኑ የኢትዮጵያ ጀግኖች ጦር ተደመሠሠ። ኢትዮጵያን ወርሬ ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁ ያለው ዚያድ ባሬም አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ሶማሊያን እስከ ማፍረስ ደረጃ አደረሳት። ኢትዮጵያን ነክቶ የቀጠለ የለምና።
ኢትዮጵያ አሸነፈች። ዘመናዊ እና ግዙፍ የተባለውን የዚያድ ባሬን ጦር አሸነፈች ተብላ በዓለም አደባባይ ከአድዋው ድል በኋላ ዳግም ስሟ ነገሰ።
የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያንም በአንድነት በመቆም ሽብርተኛውንና ከሃዲውን ትህነግን በመደምሰስ የቀደምት አባቶቻቸውን ታሪክ እየደገሙ ነው።
በአዲስ የተመሠረተው መንግሥትም የሕዝብን አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭ ጫና ለመቀልበስ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።
እስራኤላውያን ”የራሳችንን እጣፋንታ ራሳችን እንወስናለን” በሚል መፈክር ተነሳስተው በመሥራት ዛሬ ኀያል ሀገር ለመሆን በቅተዋል፡፡
ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭና የውስጥ ጠላቶቹን በመመከት ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ከፍታዋ ለመመለስ በአንድነት ቆሟል።
በሀብተጊዮርጊስ አበይ
ምንጭነት የተጠቀምናቸው:-
ኦጋዴንና የሀገር አንድነት ሥጋቶች- ከዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ) እና
ዘታይምስ ኦፍ ኢስራኤል–ኢድዋርድ ኦገስትስ ወይልድ ቶውትስ (The
times of Israel
-Edward Augustes Wild thouts)
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m