
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣዉን የሰዉ እገታ፣ የጥይት ተኩስ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የመሰረተልማት አዉታሮች ላይ የሚፈጸም ስርቆት እና መሰል የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ በሰጡት መግለጫ በሩብ ዓመቱ ዉስጥ 18 የእገታ ወንጀሎች መፈፀማቸዉን አስታውቀዋል፡፡ የእገታ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ተይዘዉ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑንም ገልጸዋል። 17 ያልተያዙ ተጠርጣዎች መኖራቸዉንም አንስተዋል።
ኮማንደር አየልኝ የጥይት ተኩስን ለማስቀረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተኩስ የተገኘ ግለሰብ አምስት ሺህ ብር፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከተገኘ 10 ሺህ ብር እና መሳሪያዉ ለስድስት ወራት እንዲያዝ፣ ከዛ በላይ ከሆነ ደግሞ መሳሪያዉ እስከ መጨረሻ እንዲወረስ መመሪያ መዉጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም እስካሁን ከ100 በላይ ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸዉንና በገንዘብ ከ270 ሺህ ብር በላይ በቅጣት መሰብሰቡን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከፀጥታ አካል ዉጭ የግል የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን የሚከለክል መመሪያ ለማውጣት በሂደት ላይ መሆኑንም ኀላፊው አስታውቀዋል።
መምሪያ ኀላፊዉ አያይዘዉም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እየተሠራ ባለ ሥራ አንድ ግለሰብ ቤት ዉስጥ ከ7 ሺህ በላይ ጥይቶች መያዛቸዉን ጠቅሰዋል።
ከተማዋ ላይ የሚታዩ ወንጀሎችን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎችም እስካሁን ከ390 በላይ ፀጉረ ልዉጥ ሰዎች ተይዘዉ ምርመራ እየተደረገባቸዉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማዋን የሽብር ቀጣና ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ተላላኪዎችን ተከታትሎ ለመያዝ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኮማንደር አየልኝ ጠቅሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከፀጥታ አካሉ ጋር እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አዲስ አለማየሁ – ጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m