
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ዘራፊው የትህነግ ወራሪ ቡድን ዘረፋ እና ውድመት ካደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል የነፋስ መውጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንዱ ነው። ሆስፒታሉ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ የሆኑትን የሕክምና መስጫ ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ መዘረፉን ተከትሎ አገልግሎት መስጠት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።
አካባቢው ከሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን ነፃ መውጣቱን ተከትሎ ማኅበራት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባደረጉት ድጋፍም በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ዛሬ ደግሞ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑት ዶክተር መንግሥቱ እርቄ እና ጓደኞቻቸው ግምታዊ ዋጋው 350 ሺህ ብር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉን በነፋስ መውጫ ሆስፒታል ተገኝተው ያስረከቡት አቶ ደገፋው ውቤ በሆስፒታሉ የደረሰው ጉዳት በጋራ ርብርብ ካልሆነ በአንድ የተወሰነ አካል ድጋፍ ብቻ የሚሠራ አይደለም ብለዋል። ድጋፉ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለመደገፍ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
ድጋፍ አድራጊው ዶክተር መንግሥቱ እርቄ በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ ወቅት ሆስፒታሉ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ለይተው እንደሄዱ የገለጹት የነፋስ መውጫ የጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ያለው ጀምበር በገቡት ቃል መሰረት አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁስ ዛሬ ተረክበናል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከዘረፋ በኋላ እንደ አዲስ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው -ከነፋስ መውጫ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m