
ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፅናታቸው ከእናት ኢትዮጵያ ፅናት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ግርማ ሞገሳቸው እንደ ሰንደቃቸው ከፍ ያለ መሆኑን ስናስብ ኢትዮጵያ በዓለም የጀግንነት እና የፍትሕ አደባባይ ያላትን ግርማ ሞገስ እንድናስብ ያስገድደናል፡፡ ትህትናቸው፣ ፍቅራቸው እና ትዕግስታቸው የወጡበትን አብራክ ይመሰክራል፡፡
የተፈናቀሉትን ሲሰበስቡ እና የተራቡትን ሲመግቡ ላየ ርህራሄያቸው አንጀት ያላውሳል፡፡ አስፈሪነታቸው ኢትዮጵያን በሩቁ እየፈሩ የሚጠሏትን የሩቅ ዘመን ጠላቶች ያስታውሳል፡፡ ኅብረታቸው እና አንድነታቸው ደግሞ ለወዳጆቻቸው ምቾትን ያጎናጽፋል፡፡ የኅብረት ዝማሬያቸው በድምጽ ብቻ የጥላቻን ግንብ የማፍረስ ምትሃታዊ ኀይልን ታድሏል፡፡ የሞራል ከፍታቸው፣ የሥነ ምግባር ልዕልናቸው እና ኅብረ ብሔራዊ ሥሪታቸው ከኢትዮጵያ ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል ያደርጋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ለጓደኞቻቸው ያላቸውን ፍቅር እና ክብር ቀርበን ስናይ ያች ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያን ቀድመን ለማሰብ ምስል ከሳቾች ናቸው፡፡ ራሳቸውን ስለሀገራቸው አሳልፈው ለመስጠት የማያመነቱትን እነዚህን የቁርጥ ቀን ልጆች ስናስተውል በዓለም የፍትሕ አደባባይ ሁሌም ሚዛን የምትደፋው ኢትዮጵያ ትታወሳለች፡፡
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የመከላከያ ሠራዊት ኀይል በሁሉም መመዘኛ ሲለካ ሀገር በቀል የሚባል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊነት የተትረፈረፈበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እየገነባች ነው፡፡ ኩሩዋ ኢትዮጵያ ኮርቶ የሚያኮራ የመከላከያ ሠራዊት እየሠራች ነው፡፡ ለጋስ ከሆነው የኢትዮጵያ መሬት የበቀሉት እነዚህ ወታደሮች ያላቸውን በፍቅር ያለስስት ሲያካፍሉ ማየት ምንኛ ደስ ይላል፡፡ ደግሞም እጅግ ሲበዛ አመስጋኞች ናቸው፡፡
ድንጋይ ተንተርሶ፣ ጤዛ ልሶ እና አፈር ለብሶ በየጢሻው የሚያድር ወታደር ጠዋት ለግዳጅ ሲነሳ ስለምን አያማርርም ብሎ ለሚያንሰላስል አሳቢ አመስጋኝነታቸው ይገለጥለታል፡፡ በዚህ ላይ “የወታደር ምቾቱ እንግልቱ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ሕዝብ ካልራቀበት የግዳጅ ቀጣና ውስጥ የሰፈረ ወታደር የዕለት ጉርሱን ለማብሰል ተጎንብሶ እሳት ሲያነድ ለሚያይ የእኔ ቢጤ አላዋቂ ለምን ከጎረቤት እሳት አይጭሩም ያሰኛል፡፡ ግን እነርሱ የኢትዮጵያ ወታደሮች ናቸው፤ ራሳቸውን ለሕዝብ ይሰጣሉ እንጂ ከሕዝብ መቀበል መርሃቸው አይደለም፡፡ ራሳቸውን አንዴ የሕዝብ አገልጋይ አድርገው ተቀብለዋልና በሕዝብ መገልገል ፍላጎታቸው አደልም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝቡ ሠራዊቱን ቀርቦ የማየት እድል አግኝቷልና ሕዝባዊ ሠራዊት ሥሪቱ እና መለያው እየሆነ መጥቷል፡፡ በየግዳጅ ቀጣናው እህል ውኃ ይዞ የሚጠይቀው ሕዝብ በልቡ ሠራዊቱን እያነገሰ እና እያመሰገነ ተመልሷል፡፡ ሰንጋ፣ በሶ፣ ቆሎ እና ውኃ ይዞ ለመጠየቅ ወደ ሠራዊቱ የተጠጋው ሕዝብ “አፈር ስሆን” እየተባለ ኮቸሮ እና አስቃጥላ ሲጎርስ ዐይኖቹ እምባ የሚያቀሩ ደጀን ሕዝብ ከቀን ወደ ቀን ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፡፡
“ሳይደግስ አይጣላም” እንደሚባለው በትንሾች የተገፋው ሠራዊት በብዙኃኑ እቅፍ ዘንድ መጠጊያ ተዘጋጅቶለታል፡፡ የሕዝብ ፍቅር ለወታደሩ ከምንም በላይ የተዘረጋ የማዕረግ እድገት ሆኖ ሲቀርብ እያየን ነው፡፡ ትናንት የክህደት ሰለባ የሆኑ ጥቂት ወታደሮች ዛሬ እልፍ ሆነው እየመጡ ነው፡፡ የመከላከያ ትምህርት ቤቶች ዛሬ በየቀኑ በብዛት በሚተም ሠራዊት የሚፈልቅባቸው ምንጮች ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ትናንት በክህደት ጥቂት ወታደሮቿን አጥታ ዛሬ በፍቅር ብዙ ሠራዊት እያፈራች ነው፡፡ በጨለማ ዘመን አልፋ ብርሃንን ከሩቅ ተስፋ የምታደርገው ኢትዮጵያ በአምሳሏ የጨለማው ዘመን ተገፎ የብርሃን ዘመን እንደሚኖር የሚያምኑ ሩቅ አሳቢ ወታደሮችን እየሠራች ነው፡፡
ከፊታቸው ስላለው ጦርነት ሳይሆን ከድል ማግስት በጦርነት የተጎሳቆለውን ሕዝብ ስለሚክሱበት ነገን በጉጉት ያልማሉ፡፡ ነገ የአቅመ ደካሞችን ቤት ሲጠግኑ፣ ነገ የነገ ተስፋ ሕፃናትን ትምህርት ቤት ሲሠሩ እና ነገ የአርሶ አደሩን ሰብል ሲከውኑ ማየትን አብዝተው ይናፍቃሉ፡፡ የእነዚህ ወታደሮች ጭንቀት ጠላቶቻቸውን ስለሚያሸንፉበት ዛሬ ሳይሆን ወገኖቻቸውን ስለሚክሱበት ነገ ነው፡፡ እሳት ጎርሶ እሳት የሚተፋ መሳሪያ የታጠቀ ሠራዊት በትዕግስት እና በብስለት ነገን አርቆ ሲያይ እንደመመልከት ድንቅ ነገር የለም፡፡ በቃ! በዚህ ሁሉ መመዘኛ መካከል ማለት የሚቻለው “ኢትዮጵያን በብዙው የመሰለ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየተገነባ ነው” በመጨረሻም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተስፋ እንደሚያደርገው፣ እንደሚመኘው እና እንደሚሽተው ኢትዮጵያን ወደ ቀደምት ልዕልናዋ ለመመለስ ብቸኛው አማራጭ ትውልዱ ይንን ሠራዊት ሲቀላቀል ብቻ ነው፡፡
ነገ ላይ ደርሳ ማየት የምትፈልጓት ኢትዮጵያ ዛሬ በዚህ ሠራዊት መካከል ጸንታ ትታያለችና ኑና እናንተም እየተመላለሳችሁ ቀደምቷን ኢትዮጵያ ከገነባችሁት ሠራዊት መካከል ጎብኟት እንላለን፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m