
❝መንግሥት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ እርምጃዎችን በፍጥነት በመውሰድ የሕዝቡን ስቃይ ማስቆም አለበት❞ ከወልድያና አካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖች
መስከረም 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አርሂቡ እያለ የሚያጎርሰው፣ የራሱን አውልቆ የሚያለብሰው፣ፍቅሩ በማር የተለወሰው፣ ደግነቱ አንጀት የሚያርሰው፣ ክፋት ያልፈጠረበት፣ ደግነት የኖረበት፣ አብሮነት የሚታወቅበት ነው፡፡ አብልቶ የጠገቡ የማይመስለው፣ ስሞት እያለ የሚያጎርሰው፣ ʺአብሽር አቦ” እያለ ጭንቅን የሚያስረሳው ደጉ ወሎዬ፡፡
ወሎ የሰውና የሀገር ፍቅር፣ ክብር፣ ምስጢር ምን እንደሆነ ኖሮት ነው የሚያውቀው፣ አድርጎ ነው የሚያሳዬው፡፡ ለፍቅር መሰጠት፣ ስለ ፍቅር መሞት፣ ስለ ሀገር ክብርና ስለ ነጻነት ራስን መስጠት ያውቅበታል፡፡ ሰዓት ሳይሸራርፍ፣ ደከመኝ ብሎ ሳያርፍ ለአዛን እየገሰገሰ፣ ሶላት እያደረሰ፣ በሸህ ሁሴን ትንቢት፣ በዱበርቲዎች ዱዓና ጸሎት፣ በግሸን ደብረ ከርቤ፣ በቅዱስ ላልይበላ፣ በሐይቅ እስጢፋኖስ፣ በተድባበ ማርያም በገደማቱና በአድባራቱ፣ በመስጅዱ በረከት በሙሐባ የሚኖር ነው፡፡ የወሎ አድባር አይከፋም፣ አያስከፋም፡፡ ፈጣሪውን እየለመነ ሀገርና ሕዝብ በፍቅር እንዲኖር የሚያደርግ ነው እንጂ፡፡ ወሎ እንኳን ሰው ጭሱ በኢትዮጵያ ሰንደቅ የሚደምቅ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠብቅ ነው፡፡
ሰንደቁ በልባቸው፣ በነብሳቸው፣ በሕይወታቸው ሁሉ እየኖረ፣ በቀያቸው እየተውለበለበ፣ አልበቃ ቢላቸው ጭሳቸውን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ያለብሱታል፣ በግርማ ያስውቡታል፡፡ ሀገሬውን በሰንደቁ ፍቅር ይጠሩታል፡፡ የወሎን ምድር የረገጠ ኹሉ ምነው ባልተመለስኩ፣ ኑሮዬንም ሞቴንም ከእነርሱ ጋር ባደረኩ ይላል፡፡ ፍቅራቸው ያስራል፣ ሊለዩ ያስፈራል፡፡ ሳይሰስቱ ይወዳሉ፣ እስከ መጨረሻው ይታመናሉ ወሎየዎች፡፡
ኢትዮጵያዊነት፣ ደግነት፣ ጀግንነት፣ አብሮነት የወሎዬ መልኮች፣ ገጾች፣ የማይለዩ ማሕተሞች ናቸው፡፡ ለወሎዬ መከፋት፣ መገፋት አይሆንም፡፡ ጭንቅን የሚያርቅ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ፣ የደበዘዘውን የሚያፈካ፣ የቀዘቀዘውን የሚያሞቅ ነውና ወሎ ሲያዝን ፍቅር ያዝናል፣ ወሎ ሲከፋ አብሮነት ይከፋል፣ ወሎ ሲተክዝ መቻቻል ይተክዛል፡፡ ውሎ ሲገፋ ደግነት ይገፋል፣ ክፋት ይሰፋል፡፡ ፍቅር እንዲሰፋ፣ መቻቻል እንዲፋፋ ወሎ በፍቅር፣ ወሎ በክብር መኖር ይገባዋል፡፡ የደጋጎች ሀገር፣ የጎበዛዝቱ እና የወይዛዝርቱ መንደር ዛሬ ላይ ተከፍቷል፡፡ ቀየውና አድባሩ መልካም ነገር የለበትም፡፡ ደጋጎቹ ተከፍተዋል፡፡ ወሎ ዛሬ ፍቅሩን፣ ክብሩን፣ ሰላማዊ ሕይዎቱን፣የሞቀ ቤቱን፣ የተመቻቸ አብሮነቱን ተነፍጓል፡፡ አርሂቡ እያለ እንግዳ የሚያገባበት፣ የተራበ የሚያጎርስበት፣ የደከመ የሚያሳርፍበት፣ ያዘነ የሚያጽናናበት፣ የተቸገረውን ቀን የሚያወጣበት ቤቱ ጎድሏል፡፡ ከሞቀ ቤቱ ተፈናቅሏል፣ ከቀዬው ተሰዷልና ወሎን ከፍቶታል፡፡ በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ግፍ ተፈጽሞበታል፡፡ ልጆቹን አጥቷል፣ ሀብቱን ተዘርፏል፣ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በወሎ ምድር ላይ በደሎችን ፈጽሟል፤ አሁንም እየፈጸመ ነው፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ወሎ ዞንና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በደልና ግፍ እየፈጸመ ነው፡፡ በደሉ በወልድያ ከተማ የከፋ እንደሆነ በደልና ግፍን ሽሽት ከወልድያ ከተማ የወጡ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በወልድያ ከተማ ሕዝቡ በጣም ተቸግሯል፣ በሀገሩ ላይ ተሳቅቆ ነው የሚኖረው፣ መውጣት መግባት ከባድ ነው፣ አሸባሪውና ዘራፊው የትህነግ ቡድን ሌሊት ሌሊት ቤት ውስጥ እየገባ ይዘርፋል፣ ወልድያ ከተማ ላይ ምንም ነገር የለም፣ ከተማይቱ ወድማለች፣ በከተማዋ ትጠቅማለች የተባለችውን ኹሉ ወደ ትግራይ ጭነዋል፣ ከአካባቢው እስኪዎጡ ድረስ በየግለሰብ ቤት እየገቡ እየዘረፉ እየጫኑ ነው ብለውናል፡፡ በከተማዋ የተገኙ ወጣቶች ታፍነው ተወስደዋል፣ እስካሁን ድረስ የት እንደደረሱ አይታወቅምም ነው ያሉት፡፡ በወልድያ ከተማ ከትንሿ ክብሪት ጀምሮ የሚሸጥ ነገር የለም፣ የነጋዴዎች እቃ ተጠቅሎ ወደ ትግራይ ተጭኗልም ብለዋል፡፡ የከተማው ሰው በእጁ ያለውን ነገር ጨርሷል፣ ብዙዎች ረሃብ ላይ ወድቀዋል፣ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በመድኃኒት እጥረት ምክንያት የመሞቻቸውን ቀን እየተጠባበቁ ነው ሲሉም በከተማዋ ያለውን ሰቆቃ ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተስፋውን የጣለው የከተማዋ ሕዝብ ቀኑ እየጨመረ ሲሄድ ከተማዋን እየለቀቀ መውጣት አማራጭ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ የአሸባሪው ቡድን አባላት በከተማዋ እየሰከሩ ሕዝቡን እንደሚሰቃዩም ገልጸዋል፡፡
በወልድያ ከተማ ሕዝብ ከዚህ በላይ የከፋ ግፍ ለመፈጸም እንደሚፈልጉና ቀን እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ ከግፍ ሽሽት የወጡት ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ምግብ በመካከል አልቆ ለከፋ ችግር እንዳይወድቁ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይመገቡ ነበር፡፡ ከከተማዋ ሲወጡ ለልጆች የያዙትን የጉዞ ስንቅ ሳይቀር እንደቀሟቸውም ተናግረዋል፡፡ በግፍ የተደፈሩ ሴቶች መኖራቸውንም ነግረውናል፡፡
በመንገዳቸው የገዢው መንግሥት ደጋፊ ነህ ብለው የያዙትን አንድ ወጣት በከፍተኛ ፍጥነት ከሚሄድ መኪና ላይ ወርውረው በመጣል በግፍ ሲገድሉት በዓይናቸው ማዬታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ልጁን ከመኪና ወርውረው ሲገድሉት ያዩ ሕጻናት ልጆች ሌሊት እየጮሁ እንደሚነሱና አልረሳ እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡ ከሰሞኑ የመጡት ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የመግባት እድል እንዳላገኙና ችግር ላይ መውደቃቸውን ነው የገለጹት፡፡ ነዋሪዎቹ የወገኖችን ስቃይ የሚያስቀረው በተባበረ ክንድ ወራሪውን ቡድን ከምድረ ገጽ በማጥፋት ሀገርን ነጻ ማውጣት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ እናቶች ሲደፈሩ፣ አዛውንቶች ሲገረፉ እያየን እንቅልፍ ሊይዘን አይገባም፣ በተለይም ወጣቱ ለሀገሩ መስዋእትነት መክፈል ይገባዋልም ብለዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ከተሞች ባዶ ቀርተዋል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃዎችን በፍጥነት በመውሰድ የሕዝቡን ስቃይ ማስቆም አለበትም ነው ያሉት፡፡ ጠላት የሚደመሰስበትን፣ ነዋሪዎችም ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትን መንገድ ማሳለጥ ይገባል እንጂ፡፡ አርሶና አንደፋርሶ የሚጎርሰውና የሚያጎርሰውን ሕዝብ በሰው እጅ ማጥገብ አይቻልም፣ ደስታውንም መተካት አይታሰብም፡፡ በጋራ ዘምቶ፣ ጠላትን በተባበረ ክንድ መትቶ መቅበር፣ ደስታቸውንም በድጋሜ መመለስ ይገባል እንጂ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m