የአማራ ክልል የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ሲያሰለጥናቸው የቆየውን 311 የቅድመ ሥራ እጩ ዐቃብያነ ሕግ እና ዳኞችን አስመረቀ።

403

የአማራ ክልል የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ሲያሰለጥናቸው የቆየውን 311 የቅድመ ሥራ እጩ ዐቃብያነ ሕግ እና ዳኞችን አስመረቀ።

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ሲያሰለጥናቸው የቆየውን 311 የቅድመ ሥራ እጩ ዐቃብያን ሕግ እና ዳኞችን በባሕር ዳር ከተማ አስመርቋል።

ኢንስቲትዩቱ ለ13ኛ ዙር ነው 311 የቅድመ ሥራ እጩ ዐቃብያን ሕግ እና ዳኞችን ያስመረቀው፤ ከእነዚህ ውስጥ 95 ተመራቂዎች ሴቶች ናቸው።

ከተመራቂዎች መካከል ወንጌል ዘገየ በቆይታቸው በዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የቆዩትን ትምህርት በተግባር በማስደገፋቸው ለሥራ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። ለማኅበረሰቡም ፍትሐዊ አገልግሎት በታማኝነት ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ሌላው ተመራቂ ዳንኤል በዛብህ በስልጠና ቆይታቸው የነበረባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት እንዳገዛቸው ተናግረዋል። በሚመደቡበት ተቋም ውስጥ ፍትሐዊና ተዓማኒ በመኾን ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ እንደኾኑም ተናግረዋል።

በኢንስቲትዩቱ በነበራቸው የስልጠና ቆይታ በአመለካከትና በክህሎት በቂ ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውን ነው የተናገሩት።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን ኢንስቲትዩቱ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕጎች እና ሌሎች የፍትሕ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና የሙያ ሥነምግባር ይዘው ኅብረተሰቡን የሚያረካ የፍትሕ አገልግሎት እንዲሰጡ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በሕገ መንግሥት ወይም በሌላ ሕግ መደንገጋቸው ብቻ በራሱ ለመብቶች መረጋገጥ ዋስትና ሊሆን አይችልም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ
ሙያዊ ነፃነት ያለው መርህን መሠረት አድርጎ የሚወስን ለእውነት የቆመ ቁርጠኛ ባለሙያ መሆንን ይጠይቃልም ብለዋል።

ተመራቂዎች ስልጠናው ይህን ብቃት እንዳስገኘላቸው እምነታቸው እንደኾነም አቶ አብዬ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ “ባገኛችሁት ስልጠና የማኅበረሰባችሁን ችግር መፍታት መቻል አለባችሁ፤ ሙያዊ ሥነ ምግባራችሁን ጠብቃችሁ በተመደባችሁበት ተቋም ለሚገጥማችሁ ችግር ኹሉ መፍትሔ መስጠት ይገባችኋል፤ ነገሮችን ኹሉ በምክንያት መርምሩ፣ አመዛዝኑ ከዚያም በኋላ ወስኑ” ብለዋል። ሁሉንም ውጣውረድ ተቋቁመው ለምረቃ ለበቁ የፍትሕ ባለሙያዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የአማራ ክልል የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ እና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ አበራ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን፣ የማኅበራት ነገረ ፈጆችን እንዲሁም የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞችንና የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ ለ 11 ሺህ 631 ዜጎች የሥራ ላይ አጫጭር ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለ12ኛ ዙር 3 ሺህ 303 ሰልጣኞች የቅድመ ሥራ ስልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል። በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ከአፋርና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለተውጣጡ የቅድመ ሥራና የሥራ ላይ ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በሕዝቡ ላይ ጉዳት በማድረሱ ተመራቂዎች የኅብረተሰቡን የሥነ ልቦና ጉዳት በመገንዘብ በትዕግስት ሕዝቡን ማድመጥና በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ፍርድን መስጠት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረጻድቅ “ተመራቂዎች በሥራ ዘመናችሁ ሁሉ ሙያን በክህሎት፣ በማንበብ፣ በሥነምግባር ማሳደግ ይጠበቅባችኋል” ሲሉ ገልጸዋል።

ባለጉዳይ ወደ ፍትሕ ተቋም ሲመጣ ፍትሕን አጥቶ በተለያዩ ነገሮች የተጎዳ በመሆኑ በማዳመጥና በትሕትና እና በትጋት ማስተናገድ ይኖርባችኋል ነው ያሉት። ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በገለልተኝነትና በፍትሐዊነት ማገልገል አለባችሁም ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በስልጠናው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት ቦታዎች ሹመቶች ሰጡ:-
Next article❝መንግሥት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ እርምጃዎችን በፍጥነት በመውሰድ የሕዝቡን ስቃይ ማስቆም አለበት❞ ከወልድያና አካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖች