ሽብርተኛው ትህነግን ማስወገድ እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ በአዲስ የተመሰረተው መንግሥት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ የታሪክ መምህራን ገለጹ።

145
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ሽብርተኛው ትህነግን ከኢትዮጵያ አስወግዶ በግፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በአጭር ጊዜ ሊመልስ እንደሚገባ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የታሪክ እና የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህራን ገልጸዋል።
የታሪክ መምህሩ ጥላሁን አስራት የትላንት አያቶቻችን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ነጻ አውጥተው የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ ትልቅ ዋጋ መክፈላቸውን አንስተዋል፡፡ ባንዳዎች ደግሞ ጣሊያን ኢትዮጵያን እንድትገዛ በር በመክፈት ሠርተዋል፤ ዛሬም ሽብርተኛው ትህነግ የፈጸመው ክህደት ይኸው ነው ብለዋል፡፡
በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በአማራ ክልል የደረሰው አሰቃቂ ድርጊትና መፈናቀል የከፋ ነው ብለዋል የታሪክ መምህሩ ጥላሁን፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ሥነ ልቦናቸውን ልንጠግን፣ ሀዘናቸውን ልንካፈል፣ ያለንን ልናካፍል እና እስኪቋቋሙ መንግሥት ያላሰለሰ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓልሞ የተነሳው የሽብር ቡድኑ ብቻ ሳይሆን ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ምዕራባዊያንም ጭምር እንደሆኑ ሁሉም ሊረዳ ይገባል ያሉት ሌላኛው የታሪክ መምህር እንዳልካቸው ደማስ ናቸው።
የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህሩ ሰይድ መብሬ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ዜጎች በግፍ ከመፈናቀል ባለፈ የሚከፈለው ሰብዓዊ ኪሳራ ነውና በአዲስ የተዋቀረው መንግሥት ለነገ ሳይል ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሽብርተኛው ትህነግ በአማራና በቅማንት ሕዝብ መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ሴራ ሲሠራ እንደነበር አንስተው መንግሥት እርስ በእርስ የሚያናክሰውን እና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈረውን የትህነግ የሽብር ቡድን አደብ ሊያስይዘው እንደሚገባ ነው የታሪክ መምህራን የተናገሩት።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ- ከገንዳ ውኃ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር!❞ የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የዘወትር መፈክር!
Next articleአሸባሪው ትህነግ በሰሜን ወሎ አካባቢዎች እያደረሰ ያለው ግፍ በተፈናቀሉ የዓይን እማኞች አንደበት…