ከ2ሺህ 500 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ግሸን መናኸሪያዎች ገብተዋል፡፡

282

እስከ መስከረም 18/2012 ዓ.ም ድረስ 2ሺህ 500 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ መናኸሪያዎች መግባታቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የተሽከርካሪ ፍሰቱን ጤናማ ለማድረግም ከዞኑ የተውጣጡ ትራፊክ ፖሊሶች ወደ ሥራው ተሰማርተዋል ብሏል ፖሊስ መምሪያው። በየዓመቱ ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 21 የሚከበሩትን የመስቀልና የግሸን ደብረ ከርቤ በዓላት ለመታደም ከሀገር እና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ የሀይማኖቱ ተከታዮች ወደ ሥፍራው ያመራሉ። ባለፈው ዓመት ከ1ሚሊዮን በላይ የሀይማኖቱ ተከታዮች በክብረ በዓላቱ እንደታደሙ ተገልጧል። በዚህ ዓመትም ከ 3 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል።
የሀይማኖቱ ተከታዮች ወደ ስፍራው ሲያመሩ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ።

በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ አበባ – ኮምቦልቻ ልዩ የበረራ አገልግሎት አመቻችቷል። ከወሎ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበርም ከኮምቦልቻ – ግሸን የመኪና መጓጓዣ አዘጋጅቷል። በሌላ በኩል ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ከተሽከርካሪ አገልግሎት ሰጪ ማኅበራት ጋር ውል በመያዝ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ግሸን የሚያመሩት ወደ ሥፍራው ከሚሄዱት የሀይማኖቱ ተከታዮች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።

የሕዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪ ፍሰቱ ጤናማ እንዲሆን ከደቡብ ወሎ ዞን የተውጣጡ 40 የትራፊክ ፖሊስ ባለሙያዎች የግሸን ደብረ ከርቤ ተጓዥ ተሽከርካሪዎችን እያስተናገዱ መሆኑን በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት የሥራ ሂደት መሪ ኮማንደር ሰይድ ሙሄ ለአብመድ ተናግረዋል። እስከ መስከረም 18/ 2012 ዓ.ም ድረስ ከ2ሺህ 500 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ተዘጋጁት መናኸሪያዎች መግባታቸውንም ተናግረዋል።

የመልከዓ ምድሩ ተራራማና ተመዝማዛነት ከመንገዱ ጠጠር መሆን ጋር ተዳምሮ የትራፊክ ፍሰቱን ፈታኝ እንዳደረገው ኮማንደር ሰይድ ነግረውናል።

አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተራራማ ቦታ ላይ ተንሸራትቶ ወደ ገደል መግባቱን፣ በተሳፋሪዎች ላይ የደረሰ የአካልም ሆነ የህይወት ጉዳት አለመኖሩንም ገልጸዋል።

የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል እስከሚጠናቀቅም የትራፊክ ፖሊስ አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ – ከግሸን ደብረ ከርቤ

Previous article40ኛው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ጉባኤ በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ እየተወያዩ ነው።