❝ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር!❞ የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የዘወትር መፈክር!

258
መስከረም 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ ስለኢትዮጵያ የሚነግረን አንድ እውነት አለ፤ የተፈተነች ሀገር መሆኗን። ትናንት የቦንብ አረር እንደ ዝናብ ወርዶባታል። ጀግኖች የመድፎችን ድምፅ ጸጥ አሠኝተዋል፤ እየተሠው መድፈኛውን ጠላት ሠውተዋል። ተዋድቀዋል!
ለግፈኛ ወራሪዎች እልፍ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር እያሉ ተሰውተውላታል። ጀግናው አፄ ቴዎድሮስ ሽጉጡን የጠጣላት ለመሆኑ ምንያህል ቢወዳት ነው? ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከዙፋኑ ያስበለጠው እስከ መስዋእት የደረሰ የክብር ሞትን ነው። በህያው ኪነጥበባዊ መወድስ ዛሬም ድረስ ትውልዱ እንዲህ እያለ የሚዘክራቸው በምክንያት ነው:-
እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፣
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ፣
አያውቅም እንዴ ክንዴ እንደሚያነድ።
በክብር መሰዋታቸውን ሕዝብም እንዲህ ሲል ክብሩን ገልጾላቸዋል።
መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ!
እንግሊዞች ንጉሡን ለመያዝና በሀገራቸው ዝናን ለማትረፍ ማርከው መውሰድ ዓላማቸው ነበርና ይህም ባለመሳካቱ እንዲህ ተብለዋል።
ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለም በእጃቸው፣
ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው፣
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው።
ኢትዮጵያ ሚስጥሯ ብዙ ነው። በየዘመኑ ያሉ ጀግኖች የኢትዮጵያን የጀግንነት ታሪክ ለማስጠበቅ እኔ ልሰዋልሽ ከማለት ውጭ ለሌላ ውሳኔ አላመነቱም።
ብልሁ እና ጀግናው ንጉሥ ምኒልክም ጠላቱን በግንባር የተፋለመ የዓድዋ ደማቅ ድል አባት ነው። እንዲህም የተባለላቸው በምክንያት ነው:-
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሃበሻ።
ጀግናዋ ሴት ጣይቱ ደግሞ ትለያለች። አንደበቷም ርቱእ ነው። ብርሀን ዘኢትዮጵያ ጣይቱ ብጡል ጠላትን የተፋለመችው ፊትለፊት ነበር። ብልህነቷ እና አስተዋይነቷ ዛሬም የአዕምሯችን ስንቅ ነው።
በላይ ገና ስሙ ሲነሳ ጠላት ይርበደበዳል። ለባንዳ ልቡ አይራራም። ጠላትን ሳያጠፋ አያድርም። ወጣት ቢሆንም ከሀገር ፍቅር ውጭ ሌላ ያሳሰበው ነገር አልነበረም። ጀግናው ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ከድል በኋላም ባመነበት ጉዳይ ተሠዋ እንጅ ከክብሩ ዝቅ አላለም።
የቴዎድሮስ እና የምኒልክ ውርሶች ነን!
እንደጣይቱ ልበ ብርሀኖች የበላይ አደራ ያለብን!
መልክና ቋንቋችን ቢለያይም ዛሬም ልባችን አንድ ነው።
በአንድነት እየቆምን በጀግንነት ጠላትን መፋለም ነው።
የልባችን ማህተም ምልክቱ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ብዙዎች ኢትዮጵያን ያስቀደሙበት ታሪክ የዛሬዎቹን እኛን የሚቀሰቅሰን የማያስተኛ ጥሪ ነው። ዛሬም ይህ ታሪክ እየተደገመ ነው። በባለ ኅብረ ቀለማዊ ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት አኩሪ ታሪኩ እየተደገመ ነው።
በርካቶች እኔስ እሞታለሁ ለሀገሬ እያሉ ወደ ግንባር እየተመሙ ነው። ሀገር ሞታ ከምታለቅስ እኔ ሞቼላት በክብር ብሰዋ ክብር ነው የሚሉት ዛሬም ማሸነፋቸውን ቀጥለዋል! በመስዋእትነት የፀና ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት !
በሀብተጊዮርጊስ አበይ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አቀረበ።
Next articleሽብርተኛው ትህነግን ማስወገድ እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ በአዲስ የተመሰረተው መንግሥት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ የታሪክ መምህራን ገለጹ።