
መስከረም 27/2014 ዓ.ም(አሚኮ) በአማራ ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብ ዓላማ ያደረገው የፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተካሂዷል።
በወዳጅነት ጨዋታውም ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ እንደተናገሩት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት በጎ ፈቃደኞች እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ይህ የበጎነት እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍና እገዛ ትልቅ የህሊና ስንቅ ከመሆኑም በላይ በአስቸጋሪ ወቅት ወገን ለወገን ያለውን መረዳዳት በተግባር የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል።
በቀጣይም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ያስችል ዘንድም ገቢ ማሰብሰቢያ መርኃግብር በስፋት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጸሐፊ እና የውድድሩ አዘጋጅ አቶ መኳንንት ደነቀው በበኩላቸው አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል በፈፀመው ወረራ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አድርሷል።
በዚህም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ድጋፍ ለማድረግ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ሰፊ እንቅስቃሴ እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወቅታዊ ሁኔታው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝም የአማራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የገቢ ማሰባሰቢያ ስፖርታዊ ውድድሩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የዛሬውን ጨምሮ በቀጣይ በሚደረጉ የስፖርታዊ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፊታችን እሁድ የአዲስ አበባ የሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታም በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንዲካሄድ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባሕር ዳርና አካባቢው ነዋሪዎች ጨዋታውን በመታደም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ጨዋታ ሰብዓዊነትን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ መሆናቸውን አንስተው፤ ለቡድኖች ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም እግር የኳስ ግጥሚያን ጨምሮ የሩጫ ውድድሮች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አምበል አምሳሉ ጥላሁን በበኩሉ ጨዋታው ለተፈናቃሉ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመሆኑ እንዳስደሰተው ገልጿል።
ለዚህ በጎ ዓላማ በስታዲም በመታደም ጨዋታውን የተመለከቱ ደጋፊዎችን አመስግኖ፤ ሌሎች የእግር ኳስ ክለቦችም በመሰል የበጎ ተግባር ዓላማ እንዲሳተፉ ጠይቋል።
የኢትዮጰያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሆነው ሃይሌ ገብረተንሳይ በበኩሉ በዚህ የበጎ ተግባር ሥራ ለሚውለው የእግር ኳስ ጨዋታ በመሳተፉ ኩራት እንደተሰማው መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m