
አዲስ አበባ: መስከረም 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ልዑክ አምባሳደር ባርሊ ሻሮን ከተመራው የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም አቶ ደመቀ ሁለቱ ሀገራት በመከባበርና እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል። ሀገራቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል።
በግብርና ምርታማነት፣ አቅም ግንባታ፣ በሰላም እና ደኅንነት ዘርፎች የጋራ ትብብሮች እንዲጠናከሩ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አዲስ መንግሥት መመስረቱን አስመልክቶም ለልዑካን ቡድኑ አባላት አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ በተጻረረ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት እስራኤል ድጋፍ እንድትሰጥ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡
አምባሳደር ባርሊ ሻሮን ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አጠናክራ እንደምታስቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m