❝አዲስ ተሿሚ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በመረዳት መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል❞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ

100
መስከረም 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንት ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 1ኛ ልዩ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አቅራቢነት አዲስ ሚኒስትሮችን ሾሟል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሃቢብ ሰይድ ካሁን ቀደም ባልተለመደ መልኩ አዲሱ መንግሥት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ስልጣን ማምጣቱ የሚደነቅ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይህም ከወቅቱ ሀገራዊ ጉዳይ ጋር የሚመጣጠንና የመንግሥት ቁርጠኝነት የታየበት ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ተመራማሪው የሚኒስትሮቹ ሹመት ስብጥር ያለው መሆኑ ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ አጋዥ ነው ብለዋል። በመንግሥት እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መቀራረብን እንደሚፈጥርም አመላክተዋል፡፡
ስብጥሩ የሐሳብ ብዝኃነት እንዲሰተናግድ ያግዛል ነው ያሉት አቶ ሃቢብ።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ ሚኒስትሮቹ በቀጣይ የሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በፍጥነት እንዲቀለበስ፣ የተዛባ ትርክት እንዲስተካከል፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር እና መሰል ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አበክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሌሎች አደረጃጀቶችም ከመንግሥት ጎን በመሆን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዲመሰረት ማገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
❝ሥልጣን በሕዝብና በመንግሥት ሃብት መገልገል ሳይሆን ሕዝብን ማገልገል ነው❞ ነው ያሉት አቶ ሃቢብ አዲሶቹ ሚኒስትሮች ሌብነትን በመጸየፍ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መፍትሔ በመስጠት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም በአማራ ክልል በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመት ማጋጠሙን ያነሱት መምህር ሃቢብ ሚኒስትሮቹ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ከእንግልትና ስቃይ ሊታደጉአቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ተሿሚ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በመረዳት መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሃቢብ፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝በሽብርተኛው የትህነግ ቡድን የተወረሩ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ድጋሜ የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን እንሠራለን❞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አልጋወራሽ ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።