❝በሽብርተኛው የትህነግ ቡድን የተወረሩ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ድጋሜ የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን እንሠራለን❞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት

361
መስከረም 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሕዝቡ፣ ወጣቶች፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የሕዝባዊ ሠራዊት በጀግንነት እየተፋለሙ እና አኩሪ ጀብዱ እየፈጸሙ ነው፡፡ እስካሁን በተደረጉ አውደ ውጊያዎችም ሽብርተኛው እና ወራረሪው ትህነግ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ከጉና እስከ ገረገራ በነበረው አውደ ውጊያ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ከንቱ ምኞት መክኖ ሙት፣ ቁስለኛ፣ ምርኮኛ ሆኖ እና ቀሪዎቹ እየተንጠባጠቡ ወደ ኋላ እንዲሸሹ ተገደዋል፡፡
የሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኘውን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት እና ቀሪ የሽብር ቡድኑን ለመልቀም ያለው ወታደራዊ ዝግጁነት ምን ይመስላል? ሲል የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን በግንባር ያሉ የሠራዊቱን አባላት አነጋግሯል፡፡
አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች በከፋ ግፍ እና መከራ ውስጥ ሆነው የእኛን መድረስ የሚጠባበቁ ወገኖች አሉን ያለችን መሰረታዊ ወታደር አበበች ዓለሜ የወታደሩ ዝግጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወገኖቻችንን ነፃ ማውጣት ነው ብላለች፡፡
የሠራዊቱ ዝግጅት ለሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች ሆነው ጠላትን የሚያሰማሩ ተላላኪዎችን ጭምር ለመቅጣት ነው ያለን ደግሞ ሃምሳ አለቃ ወሰን ባየ ነው፡፡
የሁልጊዜም የሠራዊቱ ደጀን እና አቅም የሆነው ሕዝብ በሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ግፍ እየተፈጸመበት ነው ያለው ሃምሳ አለቃ ወሰን ያ ደጀን የሆነ ሕዝብ የሰላም አየር እና ነፃነት የሚያገኝበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ነው ያለው፡፡
ሃምሳ አለቃ ወሰን “የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚያስችል ሙሉ አቅም አለው” ብሏል፡፡
❝በሽብርተኛው የትህነግ ቡድን የተወረሩ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የሽብር ቡድኑ ድጋሜ የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን መሥራት ዓላማችን ነው❞ ብሏል፡፡
ሃምሳ አለቃ ወሰን በአጭር ጊዜ አሸባሪው ቡድን የወረራቸውን አካባቢዎች ነፃ ለማውጣት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጾ ❝ከምንፈልገው ድል ለመድረስ በቂ ዝግጅት አድርገናል❞ ነው ያለው።
ሕዝቡ የምግብ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የቁሳቁስ ድጋፍ በማቅረብ ላሳያቸው ወገናዊ ድጋፍ እና አጋርነት ምስጋናውን በቃል መግለጽ አልችልም ብሏል፡፡
“ሠራዊቱ አሸናፊ መሆኑን ከጉና ሰንሰለታማ ተራሮች እስከ ደብረ ዘቢጥ ወጣ ገባ አስቸጋሪ ቦታዎች ድረስ በተግባር አሳይቷል” ያሉን ደግሞ የሬጅመንት አዛዥ የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ተክሌ አጋ ናቸው፡፡
የሠራዊቱ ቅድመ ዝግጅት ትናንት የቀሩትን ርዥራዦች በመልቀም እና ነፃ ያልወጡ አካባቢዎችን በማጽዳት ብቻ አይወሰንም ነው ያሉት ሌተናል ኮሎኔል ተክሌ፡፡
ኮሎኔሉ ሠራዊቱ ትናንት በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ኪሳራ የማይደፈሩ የሚመስሉትን እና “ጠላት ጉናን እና ደብረ ዘቢጥን ከለቀቅኩ ትግራይን እንደለቀቅኩ ይቆጠራል” ያላቸውን ቦታዎች ሳይቀር መቆጣጠሩን ገልጸው ቀሪው እዳ ለሠራዊቱ ገብስ ነው ብለውናል፡፡
ኢትዮጵያ በቀላሉ ስትነካ የምትፈርስ የመሰለው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተሳሳተ ሒሳብ ሠርቷል የሚሉት ሌተናል ኮሎኔል ተክሌ ወረራው የኢትዮጵያን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት መልካም እድል ፈጥሯልም ነው ያሉት፡፡
በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ ሕዝቡ ሠራዊቱን ለመቀላቀል እያሳየ ያለው መነሳሳት መከላከያን ሕዝባዊ እና የላቀ ግዳጅ ያለበት ተቋም እንዳደረገውም ነው የተገለጸው፡፡
ከጉና እስከ ገረገራ ሕዝቡ መረጃ በማቀበል፣ ፊት ለፊት በመዋጋት፣ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል ያሳየው አጋርነት የሠራዊቱን እውነተኛ ልብ ገዝቷል ያሉት ሌተናል ኮሎኔሉ የተገኘው ድል የሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ሠራዊቱ ከፊት ለፊቱ ያለውን ግዳጅ በድል ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጁነት እንዳለው ገልጸዋል።
ሠራዊቱ እስካሁን ነፃ በወጡ አካባቢዎችም የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም እና ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን አስተውለናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከደብረ ዘቢጥ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአዲስ የተመሠረተው መንግሥት የሕዝብን ሰላም በማረጋገጥ ከድህነት የሚያወጣ መሆን እንዳለበት የጎንደር፣ የደሴና የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next article❝አዲስ ተሿሚ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ በመረዳት መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል❞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ