
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መስከረም 24/2014 ዓ.ም የተመሰረተው አዲስ መንግሥት የሕዝቦችን ሰላም የሚያስጠብቅ፣ ከድህነት የሚያወጣ፣ አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ዜጎች አምራች ኀይል እንዲሆኑ የሚያስችል መሆን እንደሚገባው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በስልክ ያነጋገራቸው የጎንደር፣ የደሴና የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ከደሴ ከተማ አቶ በየነ ፈንታ ኢትዮጵያ በልጆቿ ደም እና አጥንት ድንበሯን አስከብራ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗን ገልጸው የሕዝቦቿን ሰላም ማስጠበቅ ድንበሯን ማስከበር አዲስ ለተመሠረተው መንግሥት ትልቁ የቤት ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ በየነ አዲስ የተመሠረተው መንግሥት በሕዝብ ይሁንታን ያገኘ መሆኑ ዋነኛው መልካም እድል ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ሽብርተኛው ትህነግን በመደምሰስ፣ ሰላምን ማስፈን እና የተረጋጋች ሀገር ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ሰላሙ እንዲጠበቅለት፣ አንድነቱ እንዲበረታ፣ ድህነቱ ተወግዶ በልቶ የሚያድር ብቻ ሳይሆን አትርፎ የሚሸጥ መሆንን አጥብቆ እንደሚፈልግ ነው አስተያየት ሰጪው የጠቆሙት፡፡
አቶ በየነ እንዳሉት ጠላቶቻችን ዛሬም የማይተኙ መሆናቸውን አዲሱ መንግሥት መረዳት እና ተገቢ ምላሽ መሥጠት አለበት ብለዋል፡፡ አዲስ የተመሰረተው መንግሥት በሀገሪቱ ላይ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ብሔር ተኮር ጥቃቶችን ማስቆም ይጠበቅበታል፡፡
መንግሥት ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ስግብግብ ነጋዴዎችን በተጠና መልኩ በመለየትና እርምጃ በመውሠድ እንዲሁም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት የተጎዱትን በማጽናናት ከሕዝቡ ጎን የተሠለፉ ነጋዴዎችን ማበረታታት ይኖርበታል ብለዋል አቶ በየነ፡፡
ለዛሬ ውድቀታችን መነሻ የሆኑትን የተሳሳቱ ትርክቶች ለማረም ሠፊ የሕዝብ ውይይት ማድረግ እና ትክክለኛውን ታሪካችንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ ሕዝቡም የመረጠውን መንግሥት በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በሀሳቡ ሊያግዝ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ከጎንደር ከተማ ያነጋገርናቸው አቶ ባዩህ በዛብህ መንግሥት ባስቀመጠው ፖሊሲ እና ስትራቴጅ መሠረት ተግባራትን ሊፈጽም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አቶ ባዩህ እንዳሉት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋት አለበት፤ ማኅበረሰቡም ሥራው በተዘረጋው መስመር መተግበሩን መከታተል ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ መንግሥት የሕዝቦችን ሰላም መጠበቅ ዋነኛው እና መሠረታዊ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ እና ቀድሞ የሚሠራው ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዛሬ ውል ለሌለው ጥፋት የተጋለጥነው የአሠራር መርሆቻችን እውቀትን ሳይሆን ዘርን መሠረት አድርገው የተፈጸሙ በመሆናቸው ነው፣ በመሆኑም መንግሥት ሥራዎችን በሠለጠነ ባለሙያ ሊሠራ እንደሚገባ አቶ ባዩህ ጠቁመዋል።
አዲሱ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ የማይወክለውን ሽብርተኛው ትህነግን በመደምሰስ በአማራ ክልል የወረራቸውን ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብን ነፃ ማውጣት ለነገ የማይለው ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው መንግሥት ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያሉ ሕዝቦች እኩል አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉበትን መዋቅር መዘርጋት ይገባዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ለመጭው ትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር አዲስ ታሪክ ሠሪ ትውልድ መፍጠርም የመንግሥት ተግባር መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ “ጠላቶቻችን ሀገራችን ፈርሳለች ብለው ቢያሟርቱም ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ወደፊትም መሠረቷ የፀና፣ ቃሏን አክባሪ፣ በአዲስ አሠራር መሪ ሀገር ሆና እንድትቀጥል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ አደረጃጀቶች ዘመኑን የዋጁ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል አቶ ባዩህ፡፡
ማኅበረሰቡም ከመንግሥት ጎን በመቆም መንግሥት መንገዱን ሲሥት ማስተካከል፣ ሲሰራ ደግሞ ማገዝ፣ መደገፍ እና ማበረታታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ነዋሪው አቶ ምትኩ ከበደ የተመሠረተው መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ እና የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባሩ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
አቶ ምትኩ አዲሱ መንግሥት የውጭ ዲፕሎማሲውን ማሳደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ሰላሙን ሲያስከብር ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ጉዳዮችን ትኩረት ሠጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የሀገሪቱን ሰላም ከማወኩ በተጨማሪ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መገንባትም ጊዜ የማይሠጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው የሚጀመሩ መሠረተ ልማቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው አገልግሎት የሚሠጡ ሊሆን እንደሚገባ አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ከሁሉም በፊት ጸረ ሰላም ኀይሎችን መደምሰስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ