
ባሕር ዳር፡ መስከረም 19/2012 ዓ/ም (አብመድ) መንግሥት የመቀንጨር ስርጭትን ማስቆም ሳይቻል ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ እንደማይቻል በመረዳት ስርጭቱን ለመቀነስ የከፋ ችግር ባለባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ‹የሰቆጣ ቃል-ኪዳን› የተሰኘ መርሀ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡
ቃል ኪዳኑ እስከ 2022 ዓ.ም ከ5 ዓመት በታች ሕጻናት የመቀንጨር ስርጭትን ዜሮ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ የአማራ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ቢራራ ለአብመድ እንደተናገሩት በአማራ ክልል 27 ወረዳዎች ተመርጠው በመጀመሪያው ምዕራፍ እየተሠራባቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው የተወሰነ ውጤት ቢገኝበትም በተገቢው መንገድ ባለመሠራቱ በሚጠበቀው ደረጃ ውጤት እንዳልተገኘበት አስታውቀዋል፡፡
የመቀንጨር ስርጭትን ለመቀነስ የተካተቱ ተቋማት ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸው፤ በቂ በጀት መድበው አለመሥራታቸው እና በመንግሥት በኩል የቃልኪዳኑን አፈጻጸም እየገመገመ የመምራት ክፍተት መኖሩ ውጤቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሆን ማድረጉም ነው የተመላከተው፡፡ አካሄዱ በቅርብ ጊዜ ቢስተካከልም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ኃላፊነቱን ለክልል ተቋማት ብቻ የመተው አዝማሚያ እንደነበራውም ነው የተገለጸው፡፡ አቶ ተፈራ እንደተናገሩት ማኅበረሰቡ ስለ መቀንጨር ያለውን ዕውቀት በማሳደግ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ አልተፈጠረም፡፡ በዚህ ምክንያት የተጀመሩ ሥራዎች መጠነኛ ውጤት ቢያስገኙም አዝጋሚ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ቡድን መሪ አቶ ስሜነህ ደግሞ መቀንጨርን አስቀድሞ መከላከል ካልተቻለ መቀልበስ ስለማይቻል የክልሉ ጤና ቢሮ ስርጭቱን ለመቀነስ ከ18 የጤና ስርፀት መርሀ ገብሮች (ኤክስቴንሽን ፓኬጆች) አንዱ በማድረግ መከላከልን መሠረት ያደረገ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የክልሉ የመንግሥት የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ቢሰሩ እንኳን ስርጭቱን የመከላከል አቅማቸው 20 በመቶ ብቻ እንደሆ ነው የተገለጸው፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው በተለያዩ ተቋማት የሚሠራ ነው፡፡
13 የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በብሔራዊ ሥርዓተ ምግብ መርሀ ግብሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ የአፈፃፀም ልዩነት ቢኖረውም እስካሁን በተሠራው ሥራ ስርጭቱን ከ46 ነጥብ 3 ወደ 41 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተመላክቷል፡፡ የመቅንጨር ስርጭቱ የተወሰነ ቅናሽ ቢያሳይም በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሠረት አሁንም መቀንጨር በአማራ ክልል የኅረተሰቡ ከፍተኛ የጤና ችግር ነው፡፡
አብመድ ያነጋገራቸው ባለሙያዎቹ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ በተቀናጀ መልኩ መሥራት ካልተቻለ ከግቡ መድረስ እንደሚያስቸግር ነው ያስታወቁት፡፡ እናቶችን በእርግዝና ጊዜ የተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የደም ማነስ እና የሆድ ጥገኛ ትላትሎችን ለማስወገድ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በቅድመ ወሊድ የእናቶች ክትትል 20 በመቶ፣ ጨቅላ ሕጻናትን እንገር በማጥባት እና እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት ብቻ በማጥባት 20 በመቶ፣ ከስድስት ወር በኋላ የተመጣጠነ ምግብ በመስጠት ደግሞ 50 በመቶውን የመቀንጨር ስርጭት ማስቀረት ይቻላል ነው የተባለው፡፡
እናቶችንና ከሁለት ዓመት በታች ሕጻናትን በአግባቡ በመንከባከብ 90 በመቶ የመቀንጨር ስርጭትን መግታት ይቻላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ታዲያ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ ትኩረት ሰጥተው ሊሳተፉ እንደሚገባ ነው ባለሙያዎቹ የተናገሩት፡፡
መቀንጨርን፣ የምግብ እጥረት እና አለመመጣጠንን ለመከላከል ምርትና ምርታማነት እና የንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ ያስፍጋል፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና ኅብረተሰቡ በቁርጠኝነት መሥራትንም ይጠይቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ