
አዲስ አበባ፡ መስከረም 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚያስተዳድረው ወኪሉ ድምጹን ሰጥቷል፡፡
በምርጫዉ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለዉን አብላጫ ድምጽ ያገኘዉ የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለመምራት ሕዝባዊ ኀላፊነቱን ተረክቦ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በመምረጥ የበዓለ ሢመት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
አዲሱ መንግሥት ሕዝቡን እና ሀገሪቱን ከተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ታድጎ ያደገች እና ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያን ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው የምክር ቤት አባላት እና በምክር ቤቱ 6ኛ የምሰረታ ገባዔ የተሳተፉ አካላት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስና በክፉ አሳቢ ጠላቶቿ እጅ እንድትወድቅ እና ሕዝቦቿም የማያውቁትን ባርነት እንዲያዩ አሸባሪዉ ትህነግ በስልጣን ላይ እያለ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ከስልጣን ከወረደ በኋላም ልኬት በማይገኝለት የጭካኔ ድርጊቱ ሀገሪቱን እና ሕዝቦቿን ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለም ገልጸዋል፡፡
በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራ እና አፋር ክልሎች አዲስ የተመሰረተዉ መንግሥት ልዩ ድጋፍ ማድረግ እና ተጎጅዎችን ማቋቋም ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም እንደሆነ የተናገሩት የሕዝብ እንደራሴዎቹ እና ተጋባዥ እንግዶቹ ከአሁን በፊት ያጋጠሙ አለመረጋጋቶች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች እንዳይደገሙ መንግሥት ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ እና ሀገሪቱን ከተጋረጠባት አደጋ የማዳን ተግባሩን ሕዝብን አሰተባብሮ ሊወጣ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡
ሰላም እና መረጋጋት የሰፈነባት እንዲሁም የበለጸገች ሀገር ስትፈጠር ተጠቃሚዎቹ ዜጎች በመሆናቸዉ ከመንግሥት ጎን መሰለፍ እና ሀገራቸዉን በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸዉም የሕዝብ እንደራሴወቹ እና ተጋባዥ እንግዶቹ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m