
ደሴ፡ መስከረም 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በደሴ እና አካባቢው ተጠልለው ይገኛሉ። ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ እንደቀጠለ ነው፡፡ የፌዴራል የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ፣የአልባሳት እና የንጽህና መጠበቂያ በደሴ ከተማ በመገኘት ለተፈናቃዮቹ አስረክቧል።
የፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ ለተፈናቃዮች በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብ፣የአልባሳት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የኢትዮጲያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተሻለ በሬቻ (ዶክተር) ድጋፉ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
አሸባሪው እና ወራሪው ትህነግ ያደረሰው ግፍ አሰቃቂ እንደሆነ መመልከታቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። ካለው መጠነ ሰፊ ችግር አኳያ ሌሎች የመንግሥትም ሆኑ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ መሳይ ማሩ በደሴ ብቻ ከ350 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች እንዳሉ ገልጸው በየጊዜው ወደ ከተማዋ የሚገቡት የተፈናቃይ ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
የፌደራል ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ድጋፍ የሚመሰገን መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ መሳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የቻሉትን ድጋፍ ለወገናቸው እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሳላሀዲን ሰይድ-ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ