ወንድማማቾቹ ጀብደኞች!

516
መስከረም 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ትዕቢተኛ ምላስ ራሱን ያጠፋል፡፡ ትዕግስት ግን ፍርሐት ሳይሆን አርቆ ማየት ነው፡፡ ምናልባት ትህትናን በተላበሰ ምላስ ውስጥ ፍርሃት የማይዞረው ልብ ይኖራል፡፡ አማራ ለፈጣሪው ካልሆነ ለፍጡር መንበርከክን አብዝቶ ይጠላል፡፡ ይህ ዝም ብሎ የመጣ ማንነት ሳይሆን አብሮ የተፈጠረ መገለጫ ነው፡፡
ራስን አስከብሮ ሌሎቹን ማክበር ምናልባት ለአሸባሪው ቡድን የሚዋጥለት ባይሆንም ትልቅ ዕሴት ነበር፡፡ ገድሎ መፎከር ብቻውን ጀግንነት አይደለም፤ አንገት ደፍቶ መኖር እና ከግጭት መራቅም ፍርሃት ሊሆን አይችልም፡፡ ያለቦታቸው እና ያለሥሪታቸው ጊዜ የሰጣቸውን ከፍታ ራሳቸው ታግለው ያወረዱት የሽብርተኛው ትህነግ ቡድኖች አማራ ንቆ ሲተዋቸው ሒሳብ እናወራርዳለን ብለው ደጁ ድረስ መጡና ራሳቸውን ወደ ማይቀረው ዓለም አወረዱ፡፡
“በሒሳብ እናወራርዳለን” ቅሌት ወደ አማራ ምድር የዘለቁት ወራሪዎች በሕዝብ ላይ የሚጠገን ስብራት ቢፈጥሩም በዞረ ድምር የማይካካስ የሕይዎት ዋጋ የሚከፍለውን ግን ዓለም ለይቶ ያውቀዋል፡፡
የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው በውል ባልገባቸው እሳት ውስጥ ገብተው እየተለበለቡ ስለመሆናቸው ምናልባትም ዛሬ ባይገባቸው ነገ ግን ይገለጥላቸዋል፡፡
ትዕቢት ከክላሽ አፈሙዝ የሚወጣ እርሳስን አያበርድም፡፡ ጥላቻ የሞርተር እሳትን አይመክትም፡፡ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸም ከቢኤም እና ዲሽቃ ላንቃ የሚወረወርን ቅምቡላ አይከላከልም፡፡ እነዚህ ሁሉ አረሮች የሚያርፉት እና የሚበትኑት በጥላቻ የደነደኑትን እና በአፍቅሮ ንዋይ የዋጀጁትን የአሸባሪውን ትህነግ አባላት ገላ ነው፡፡ ይህም በዚህ ወቅት እየተፈጸመ ነው፡፡
ከሰሞኑ በመቄት እና አካባቢው “ወንድማማቾቹ ጀብደኞች” ስለፈጸሙት ገድል በአጭሩ እንንገራችሁ፡፡
ወንድወሰን አይቸው ተወልዶ ያደገው መቄት ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው ግን በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ለዚህ ወቅት ጀብዱ እድል ሆኖለታል፡፡ ትግርኛን ባይናገርም ማዳመጥን ግን በቆይታው ተክኖ ተመልሷል፡፡ ወራሪዎቹ ወደ አማራ ክልል ከዘለቁ በኋላ ሚስጥር ያሉትን ሲናገሩ አድማጭ ይኖራል ብለው አይጠራጠሩም፡፡
ነሐሴ 30/2013 ዓ.ም ለተለመደው የዘረፋ ሥራቸው ወደነወንድወሰን ቤት ያመሩት ጥንድ የሽብርተኛው ትህነግ ሽፍቶች ከዘረፋ በኋላ ግጭት ያምራቸዋል፡፡ በአማርኛ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ሁሉ የማይመች ምላሽ የሚሰጣቸው ዘራፊዎቹ ንቀቱ እንደመድፈር ተቆጥሮ ወደ ግጭት ያመራሉ፡፡ የታጠቁት መሳሪያ የሌላቸውን ልብ ይሰጣቸውና ሲዘንብ አረፋፍዶ ከራሰው መሬት ላይ ተኛ ይሉታል፡፡ ወንድወሰንም ጭቃ ላይ አልተኛም ነገር ግን የምትፈልጉትን የኀይል አማራጭ መጠቀም ትችላላችሁ ይላል፡፡ ተነጋግረው ወጣቱን ወደሚፈልጉት ቦታ ለመውሰድ ስምምነት ላይ ሲደርሱ እንደማያውቅ ሆኖ ያዳምጣቸዋል፡፡ በመጨረሻም ወደጫካ እንዲሄድ ያዙታል፡፡ ለመሄድ ሲነሳ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ዘራፊዎቹን አጥብቀው ቢለምኗቸውም የሚለመኑ አልሆኑም፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ታላቅ ወንድም መቆያ አይቸው “ታናሽ ወንድሜን ብቻውን አልክም፤ ከፈለጋችሁ ሁለታችንንም ልትወስዱን ትችላላችሁ ያላቸው፡፡”
ታላቅ እና ታናሽ ክላሽ ተደግኖባቸው ወደ ጫካ ይሄዳሉ፡፡ በመንገዳቸው ሁሉ ስለቀጣይ እቅዳቸው ሲነጋገሩ የሚያዳምጠው ወንድወሰን መግደል፣ አካል አጉድሎ መልቀቅ ወይም 10 ሺህ ብር እንዲሰጧቸው እርስ በርሳቸው ስምምነት ላይ ሲደርሱ እያዳመጠ ይጓዛል፡፡ ከሚፈልጉት ቦታ ሲደርሱም ሽፍቶቹ ሁለቱን ውንድማማቾች 10 ሺህ ብር እንዲሰጧቸው ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ወንድማማቾቹ የተጠየቁትን ብር መክፈል እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መካከል ነበር የወንድማማቾቹ አጎት የነበረው ዘላለም ኑሩ በቦታው ደርሶ በተማፅኖ እንዲለቋቸው ጥያቄ ያቀረበው፡፡ ለልመናው ከመራራት ይልቅ አቶ ዘላለም ከእነወንድወሰን ጋር ይታገታል፡፡ በመካከሉ በነበረው የቃላት መካረር ዘራፊዎቹ የሽብርተኛው ትህነግ አባላት ከቃላት አልፈው ወደዱላ ያመራሉ፡፡ ነገሩ በጣም ያናደደው አጎት አሸባሪዎቹ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ቢጠይቅም የሚለመኑ አልሆን ይላሉ፡፡
መሳሪያ ከታጠቁ እና ዓላማ ከሌላቸው ዘራፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባት ያስጠላው ታላቅ ወንድም መቆያ አጎታቸውን የጠየቁትን ብር እንዲያመጣላቸው ይነግረዋል፡፡ አጎታቸው እና ታናሽ ወንድሙ ወንድወሰን ግን ዘራፊዎቹ የጠየቁት ብር እንዲመጣ ፈቃደኞች አልነበሩምና መካረሩ እየበረታ ሲመጣ መሳሪያ አቀባብለው አጎታቸው ላይ ይደቅኑበታል፡፡
በዚህ ወቅት ነበር መቆያ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ ሁለቱ የሽብር ቡድኑ አባላት አቀባብለው ከአጎታቸው ላይ የደቀኑትን ክላሽ አፈሙዝ ቀና አድርጎ ይይዝና፤ መታገል ይጀምራሉ፡፡ ሞት እንደማይቀር የወሰነው ወንድወሰን ወንድሙ የተደቀኑትን የክላሽ አፈሙዝ ከአጎቱ ቀና አድርጎ እንደሚታገል ሲያይ ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱን ተሸክሞ በጭንቅላቱ ያቆመዋል፤ እንዳይነሳ አድርጎም በአገኘው ነገር ሁሉ ይመታዋል፡፡
አጎታቸው ከተቀመጠበት ለመነሳት ሲሞክር አንዱ ሽፍታ የሞት ሞቱን ተጣጥሮ ከተኮሳቸው ሁለት ጥይቶች መካከል አንዷ የአጎታቸውን ቀኝ እጅ ላይ ቀላል ቁስለት ታደርሳለች፡፡ ወንድወሰን ከጣለው ሽፍታ የቀማውን ክላሽ ከመቅጽበት በሁለቱ ሽፍቶች ላይ አርከፍክፎ ወደማይቀሩበት ይሸኛቸዋል፡፡ የነጠቁትን ክላሽ ይዘው ወደመጡበት ሲመለሱ የአካባቢው ሕዝብ እየሮጠ የመጣው እነወንድወሰን ሞተዋል ብሎ በማሰብ ነበር፡፡
ሕዝብ የፈራው አልሆነም፡፡ ግፈኞቹ የሞት ሞትን ሞተው እስከወዲያኛው አሸልበዋል፡፡ ወንድማማቾቹ ጀብደኞች ታጥቀዋልና ከዚህ በኋላ ከቀያቸው መሸሽ አልፈለጉም፡፡ በአካባቢው ያሉት የአሸባሪው ትህነግ ቡድን አባላት የሆነውን ቢሰሙም ወደእነወንድወሰን ቀየ ለፍልሚያ መሄድ እንደማያዋጣቸው ግን አውቀውታል፡፡ በተለያየ መንገድ በአካባቢው በመሄድ ጥቃት ለመሰንዘር ያደረጉት ሙከራም አልተሳካላቸውም።
በመጨረሻም በአካባቢው በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው የወገን ጦር ከቀናት በኋላ የማያዳግም ርምጃ መውሰድን ተከትሎ ወንድማማቾቹ ገድለው በማረኩት መሳሪያ ከወገን ጦር ጎን ሆነው ጠላትን እየቆሉ ነፃነታቸውን አወጁ፡፡
“የአሸባሪው ቡድን አባላት ጉልበት፣ ፕሮፖጋንዳ እና የታጠቁት ጥይት ነበር” የሚለው ወንድወሰን አሸባሪዎቹን በሐሰት ፕሮፖጋንዳ አግዝፎ ያየበትን ቀን ይጠላል፡፡ ከዚህ በኋላም የወገን ጦር በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት እሰከ መጨረሻ ለመፋለም እና ለመቅበር ተዘጋጅተናል ነው ያለን፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአዲሱ መንግሥት ሰላምና ደኅንነትን ከማስከበር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ በትኩረት እንዲሠራ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next articleየጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ አሸኛኘት ተደረገላቸው።