
ደሴ: መስከረም 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እንይሽ አለበል ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት አዲሱ መንግሥት ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባዋል፡፡ በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ወረራ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በኮምቦልቻ ከተማ እንደተጠለሉ የተናገሩት ነዋሪዋ በቀጣይ አዲሱ መንግሥት ከሁሉም በፊት ዜጎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ማስቻል እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
አዲሱ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባውም ነው ወይዘሮ እንይሽ የተናገሩት።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሚፍታ ኢብራሂም፣ በብዙ ችግሮች ውስጥም ቢሆን የመንግሥት ምስረታ በመካሄዱ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአዲስ የተመሰረተው መንግሥትም ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ሰላማቸው ተጠብቆ ሠርተው ሃብት የሚያፈሩበትን ሥርዓት መዘርጋት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ እምነት እንዳለው ነው የተናገረው።
አሁን ላይ በሰላም እጦት ምክንያት ኮምቦልቻ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮችን እየደገፉ እንደሚገኙ የገለፀው ወጣቱ በቀጣይም መንግሥት የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ሠርተው እንዲኖሩ ተፈናቃዮችን ማቋቋም እንዳለበትም ተናግሯል።
አዲስዓለም ከበደ የተባሉት ነዋሪ ደግሞ አዲሱ መንግሥት ሰላምን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሻሻል የኑሮ ውድነትን መቅረፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበትም ነው የተናገሩት። ነዋሪው መንግሥት ሕግ የማስከበር ሂደቱን አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ግርማ ሙሉጌታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m