
ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ገሚሶች በቅናት፣ ገሚሶች በክፋት፣ በምኞት፣ ሌሎች በአድናቆት፣ ይመለከቷታል፤ ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ዞረዋል፣ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን አይተዋል፣ የሚሆነውን ለማየት ጓጉተዋል፡፡ የቀደመችውን፣ የነጻነት አርማ የሆነችውን፣ የዓለምን የፍትሕ መንገድ የቀየሰችውን፣ በቀየሰችውም መንገድ በእኩልነት ያራመደችውን፣ እስከ መቃብር ድረስ የምታፈቅረውን፣ እስከ ሞት የምትታመነውን፣ ለምስክርነት የተመረጠችውን ሀገር የሚያያት በዝቷል፡፡ የጥቁሮች መመኪያ፣ የነጻነት ወንዝ መፍለቂያ፣ የሰው ዘር መነሻ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ ኢትዮጵያ፡፡
ከቀደሙት ትቀድማለች፣ ከገዘፉት ትገዝፋለች፣ ኃያላን ነን ከሚሉት ሁሉ ትበልጣለች፣ ለምድር የተሰጠውን ሁሉ ይዛለች፣ በረከቱ፣ ሀብቱ፣ ጽናቱ፣ አንድነቱ፣ ቀዳሚነቱ፣ አሸናፊነቱ ሁሉ ከእርሷ ጋር ነው ኢትዮጵያ፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም መሠረት፣ የፍጥረታት እናት ናት፡፡ ዓለም ከእርሷ ውጭ መሠረት የላትም፣ መሰረቷ፣ ዋልታና ማገሯ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከእርሷ በፊት የነበረ፣ ከእርሷ በፊት የከበረ፣ ከእርሷ በፊት የዳበረ የለም፡፡
በኢትዮጵያ የተበለጡ ሁሉ ስለ እርሷ መጥፋት፣ መከፋትና አንገት መድፋት ይጥራሉ፣ በየዘመናቱ ጦር ይሰብቃሉ፣ ሠራዊት ያዘምታሉ፣ በኢትዮጵያ ምድር በኢትዮጵያዊያን ላይ ነግሰው ለመኖር ይሻሉ፡፡ ዳሩ ያሰቡት አይሆንም፣ ተሸንፈው ይመለሳሉ፣ አሸናፊነት ሲመኙ ሽንፈት፣ መግደል ሲመኙ መሞት፣ ይደርስባቸውና ቆዝመው ይመለሳሉ፣ ብዙዎችም በኢትዮጵያ አፈር ተበልተው ይቀራሉ፡፡ እርሷን ነክቶ ያሸነፈ፣ የክብሯን ወሰን ያለፈ የለም፡፡ ክብሯ ኃያል ነው፣ ልኳ አሸናፊነት፣ አይደፈሬነት፣ ቀዳሚነት ነው፡፡
በጦር ዘምተው ማሸነፍ ያልሆነላቸው፣ በገንዘብ፣ በውሸትም ሊያሸንፏት ጥረዋል፡፡ ታዲያ ሁሉም ተሸንፈዋል እንጂ አንዳቸውም አላሸነፏትም፣ አያሸንፏትም፡፡ ከትናንት ወዲያ ተሸንፈዋል፣ ትናንትም ተሸንፈዋል፣ ዛሬም ተሸንፈዋል፣ ነገም ይሸነፋሉ፣ እርሷ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠረች ሀገር ናትና፡፡ በዚያ ዘመን አልሆንላቸው ያሉት የኢትዮጵያ ጠላቶች በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያን እየፈተኗት ነው፡፡ በፈተናዎች ማለፍ፣ በግጥሚያዎች ሁሉ ማሸነፍ መገለጫዋ የሆነው ድንቅ ሀገር ታዲያ ፈተናዎቿን እያለፈች ነው፡፡
በአሸባሪውና ወራሪው የተከፈተባት ጦርነት፣ የውጭ ጠላቶቿ በተሳሳተ መንገድ ኢትዮጵያን መፈረጅ፣ ማዋከብና ጫና መፍጠር፣ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና የቀጣናው ሀገራት ስግብግበነት፣ በምርጫ ወቅት የነበረው የውጭ ጠላቶቿ ግንዛቤ፣ ምርጫው እንዳይካሄድ የአሸባሪ ቡድኖች ጥረት ኢትዮጵያን የፈተኗት ፈተናዎች ናቸው፡፡ በዓመቱ የተፈተነችበትን የሕዳሴ ግድብን ሙሌት በድል አጠናቀዋለች፣ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫዋንም በድል አልፈዋለች፣ የዓለምን የተዛባ አካሄድም እያስተካከለች፣ እውነታውን እያስያዘች ነው፡፡ የቀራት የዓመታት ጠላቷን ትህነግን እና አመለካከቱን ማጥፋት ነው፡፡ እርሱን በማጥፋት ላይ ትገኛለች፡፡
ትፈርሳለች ሲሏት የጸናች፣ ተሸነፈች ሲሉ በድል የመጣች ውብ ሀገር ኢትዮጵያ ከአለፉት ሁሉ የተሻለ ነው የተባለለትን ምርጫ ካደረገች በኋላ አዲስ መንግሥት መሥርታለች፡፡ መንግሥት አትመሰርትም፣ ግድቧን አትሞላም፣ ሉዓላዊነቷንም አታስከብርም ያሏት ሁሉ ዛሬ ላይ በትዝብት እየተመለከቷት ነው፡፡ እንዴት ሆነ ሲሉም እየጠየቁ ነው፡፡ አንዳንዶች ስለሆነው ሁሉ ገርሟቸዋል፣ ስላደረገችው ነገር ሁሉ ደንቋቸዋል፡፡ ዓይኖች ሁሉ ወደ እርሷ ዞረዋል፣ በአግራሞት እየተመለከቷት፣ ጽናቷን እያደነቋት፡፡ ገሚሶቹ አንጄታቸው እያረረ፣ ልባቸው እየተኮማተረ፣ ፊታቸው እየተቋጠረ፣ በቁጭት፣ በብስጭት፣ በውርደት ነው የሚመለከቷት፡፡ በደስተዋ የሚደሰቱ፣ ደግሞ በደስታ፣ በፌሽታ፣ በእርካታ እየተመለከቷት ነው፡፡ በድሏ ኮርተዋል፣ በአሸናፊነቷ ተመክተዋል፡፡
ጠላቶች ኢትዮጵያን አያውቋትም፣ መርምረው አይደርሱባትም፣ ገፍተው አይጥሏትም፣ ተዋግተው አያሸንፏትም፡፡ ምስጢር፣ ፍቅር፣ ክብር፣ ያላትን ሀገር ማን ያሸንፋል፡፡ የምታደርገውን እያዬ በድንቅ ታሪኳ ይደመማሉ እንጂ፣ ኢትዮጵያ አዲሷን መንግሥት መሥርታለች፣ ኢትዮጵያዊያንም አዲስ ተስፋ በአዲሱ መንግሥት ላይ ጥለዋል፡፡ ወደ ፊት እንዳይራመዱ የሚጎትታቸው፣ በአንድነታቸው ላይ የሚመጣባቸውን አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ከቅድስት ሀገራቸው ተነቅሎ እንዲወድቅ የመጀመሪያው ፍላጎታቸውና ተስፋቸው ነው፡፡ ጠላት ተመትቶ ሲደመሰስ፣ የተፈናቀሉትን መመለስ፣ ቤታቸውን ማደስ፣ ደስታቸውን መመለስ የሚቀጥለው ተስፋቸውና ጥያቄያቸው ነው፡፡ ከአዲሱ መንግሥት ሰላምና ደኅንነት፣ ሀገራዊ አንድነት፣ የሞቀ ልማትም ይሻሉ፡፡ አዲሱ መንግሥት የዜጎችን ጥያቄ እንደሚመልስ ቃል ገብቷል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በጽናት፣ በትዕግስት፣ በጀግንነት ሀገራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ጠላቶችም በአሻገር እያዩ ይቆዝማሉ፣ ወዳጆችም እያዩዋት ይደሰታሉ፡፡ እርሷ አትሸነፍም፣ ክብሯን አሳልፋ አትሰጥም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው መተባበር፣ መደጋገፍ፣ በጋራ መዝመት፣ በጀግንነት መዋጋት ያውቁበታልና ሀገራቸውን አያስደፍሩም፡፡ ችግሮች ቢበዙባቸው፣ መከራዎች ቢደራቡባቸው፣ በደሎች ቢመጡባቸው በጽናት ይሻገሯቸዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m