
መስከረም 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በበዓለ ሲመታቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ከቀደሙ ድሎቻችን ጋር ሲነጻጸር ነገ ላይ የሚጠብቀን ተስፋ ቢበልጥ እንጂ አያንስምም ብለዋል፡፡ ተስፋውን አይተን እውን ለማድረግ ምን ያክል ዝግጁ ነን የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ መልካም መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትበለጽገው ሀገራችንን ለመለወጥ በፈለግንበትና የጋራ ራዕይ በሰነቅንበት ልክ ብቻ ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው፣ ይህን ለማሳካትም የዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን ታላቅ አደራ እንደተጣለባቸው ነው የገለጹት፡፡ አደራውን ጠብቀን፣ የዘመናት በጎ ድምር ውጤቶችን፣ ኢትዮጵያ የተባለችውን መርከብ ማዕበል ወጀቡ ፈጽሞ እንዳያናውጻት አድርጎ እንድትጓዝ ማድረግ የኢትዮጵያ ልጆች አደራ ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ዲሞክራሲን ለመትከል ተጋድሎ ማድረጓን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋና ስጋት፣ እድልና ፈተና፣ እየተፈራረቁባት አያሌ ውጣ ውረዶችን ተሻግራ እዚህ ደርሳችም ብለዋል፡፡
6ኛው ምርጫ ከእንከኖች ሁሉ የጸዳና እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም፣ የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዲሞክራሲዊ ሥርዓትን ከመትከልና፣ የማጽናት ሕልም እውን ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤ አንድ እርምጃም ወደፊት አራምዶናል ነው ያሉት፡፡
ስልጣን በእውነተኛ የሕዝብ ድምጽ የሚመነጭ መሆኑን ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡ በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲ ብቻ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡ ድሉ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብ በአንድነት ያሸነፉበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ድሉ ብዙ ቀዳዳዎችን መድፈን የሚያስችል ትልቅ እድል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“ለዘመናት እየተከማቹ የመጡ ችግሮች በአንድ ፓርቲ መሪነትና መፍትሔ አመንጭነት ማስወገድ እንደማይቻል ታውቆ ተደራርበው የመጡብን ችግሮች ተባብረንና ተደምረን ለማሸነፍ መነሳት ይኖርብናል፤ በእኛ በኩል በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ሕልም ለስኬት እንዲበቃ እንሠራለን” ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ሥርዓታችን የአሸናፊዎች ፍላጎት ነጸብራቅ ብቻ ሳይሆን የመግባባታችን ውጤት እንዲሆን እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡ የውስጥ ሽኩቻ የጠላት መረማመጃ አድርጎ መቆየቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳባችንን አስታርቀን፣ ልዩነቶቻችን አክብረን ሕብረ ብሔራዊነታችን አጠንክረን፣ ወደ ከፍታ የምንተምበት ጊዜ ይሆናልም ብለዋል፡፡ ይህም እንዲሳካ አካታች ብሔራዊ የምክክር መድረክ እናዘጋጃለን ነው ያሉት፡፡ ችግሩ የሚፈታው በሁሉም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊት ላይ የግፍ ግፍ እንደፈጸመ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥሞና ጊዜ ተሰጥቶ ክፉና ደጉን ያለዩ ሕጻናትን የጦር መሳሪያ አስታጥቆ፣ የሕዝብ መገልገያዎችን እየናደ፣ ቤተሰብ እየበተነ፣ ንጹሓንን እየረሸነ፣ እንስሳትን እየረሸነ፣ የሃይማኖት ተቋማትን እያረከሰ ሲወጋ ለሕልውና ዘመቻ ተገደን መግባታችን ሊሰመርበት ይገባል ነው ያሉት፡፡
“ሰልፍ ይዘን ስንዘምትም ሆነ ሰይፍ ይዘን ስንነሳ፣ ዋና ጸባችን ሀገር ሊያፈርሱ ከተነሱ ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች ጋር ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ለማለፍ ትክክለኛ አቋም ያለው የጸጥታ ኃይል እንደምትገነባም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷን ለመጠበቅ እያደረገችው ባለው ዘመቻ የክህደት ታሪክ የደገሙና ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩ ሀገራት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ወዳጅነት የኢትዮጵን ክብርና ሉዓላዊነት በሚሰዋ መልኩ መሆን የለበትም፣ ሊሆንምም አይችልም ብለዋል፡፡ በፍቅር ለሚቀርቡን ሀገራት ልባችን በራችን ሁሌም ክፍት ነው፤ እኛ ኢትዮጵያን ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የተባበረች፣ የበለጸገች፣ ሰለማዊ እና በዓለም መድረክ ጥቅሟን የምታስከብር አፍሪካን አህጉር እንድትኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንጥራለን ብለዋል፡፡ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያገናኙን ነገሮች ይበልጣሉም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
