ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በበዓለ ሲመታቸው ካስተላለፏቸው መልዕክቶች መካከል፡-

326
በኢትዮጵያ ረጅም የመንግሥት አስተዳደር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽና ተዓማኒ የሆነ ምርጫ በማድረግ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት በመመስረታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ወሳኝና ፈታኝ በሆነው ወቅት በሕዝብና በሀገር ላይ የተቃጣውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ በዱር በገደሉ ተጋድሎ እያደረጉ ላሉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
እናንተ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግና የምታካብረው ኢትዮጵያ ውለታችሁን አትረሳውም ብለዋል፡፡ የሚከፈለው መስዋእትነት በታሪክ ማሕደርና በልባችን ብራና ላይ ታትሞ ይኖራልም ነው ያሉት፡፡
እልፍ ጀግኖችን ካፈራው ሕዝብ አብራክ በመፈጠሬ ሁሌም እንድኮራ ከሚያደርጉኝ ነገሮች መካከል የሕዝቡ ጽናት፣ አይበገሬነትና አትንኩኝ ባይነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ጥቃት የሚያንገበግበው፣ ጠላት ሲመጣ ቅሬታውን ወደጎን ብሎ ሀገርን የሚያስቀድም፣ በሉዓላዊነቱ የማይደራደር ነውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሕዝባችን መተማመኛችን፣ ጦርና ጋሻችን ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድጋፍ በፈለገች ጊዜ ለደረሳችሁላት፣ አቅም ባነሳት ጊዜ ምርኩዝ ለሆናችኋት፣ በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ምስጋና አቅርበዋለሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአቃፊነቷና በቀደመመ ገናና ታሪኳ በመርከብ ትመሰላለች፣ መርከቧ ኢትዮጵያ፣ የፍትሕ፣ የእኩልነትና የላቀ ስብዕና ሀገር ናት፣ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም የተባለላትና ከቀደምት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ የሆነውን ጃንደረባ ያፈራች ናትም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ነብዩ መሐመድ የተከታዮቻቸው ማረፊያ አድርገው የመረጧት፣ የእውነትና እርትዕ ሀገር ብለው ያወደሷትና የመጀመሪያው ሟዚም ቢላል መነሻ የሆነች ሀገር ናትም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ፍትሕንና ዳኝነትን የሚያውቁ፣ ኪነ ሕንጻና ስዕሎቻቸው በጥበብ የደመቁ ተብለን የተመሰከረልን ድንቅ ሕዝቦች ነንም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በኤዞር ተረቶችና በሚናደር ተውኔቶች የተወደሰች፣ ግሪካዊ የታሪክ አባት ሔሮዳተስ የወርቃማ ባሕልና ሥነምግባር ባለቤቶች የሆኑ ብልሕ ሕዝቦች ብሎ የጻፈላት ድንቅ ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
የዘመናችን አርኪዎሎጂስቶች ምድረ ቀደምትነቷን ያረጋገጡላት፣ በጸረ ቅኝትና በአፓርታይድ ትግል ወቅት ከራሷ አልፋ፣ ለአፍሪካ ሀብቷን ቀንሳ ሳትሰስት የሰጠች፣ በጥቁር ሕዝቦች ትልቅ ልብ ውስጥ ጎልታ የተሳለች፣ አፍሪካዊ ማንነቴን የገለጸችልኝ ተብላ የተወደሰች፣ የእውነት፣ የአፍሪካዊ ሞገስ ፈርጥ ናትም ብለዋል፡፡
አትችሉም ሲሉን ከታሪክ መርከብ ገልጠን የአባቶቻችን ገድል በማጣቀስ፣ ሁለትም የእኛ ትውልድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የወጠነውን አይቀሬ ጉዞ ወደ ውጤት መቀየር መቻላችንና ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በታርቆ ክንዴ
Previous article“ኢትዮጵያ የሁሉም የአፍሪካ ሀገር እናት ነች፣ ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግናን እመኛለሁ” የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ
Next article“በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ሕልም ለስኬት እንዲበቃ እንሠራለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)