
መስከረም 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ የመንግሥት ምስረታ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኬኒያ እህቶችህና ወንድሞችህ ምርጫውን በሰላማዊ መልኩ በማሸነፍህ እንኳን ደስ አለህ ብለውሃል ነው ያሉት፡፡
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ እዚህ የቆምኩት ያለኝን ድጋፍ ለማሳየትና በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ልማትና ኢትዮጵያን ዳግም ለመገንባት ያለውን ጥረት ለመደገፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር እጅ ለእጃ ተያይዛ ለማደግ ዝግጁ ነችም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያና የኬኒያ ወንድሞችና እህቶች ቀጣናችሁን በጋራ ማሳደግ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር የኬንያ ሕዝብን ወክዬ ያለኝን ድጋፍ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ “ዛሬ በሕዝብ የተመረጣችሁ መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ እንድትመሩት፣ ሰላምና መረጋጋትን እንድትፈጥሩለት እንዲሁም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወደ አንድነት እንድታመጡት ኃላፊነትን ጥሎባችኋል“ ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ሀገርና በቀኝ ግዢዎች ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር መሆኗን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ መስክረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የሁሉም የአፍሪካ ሀገር እናት ነች፣ ሁላችንም እንደምናውቀው እናት ሰላም ከሌላት ቤተሰብ ሰላም የለውም፤ በመሆኑም ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግናን እመኛለሁ“ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ