
ደብረታቦር፡ መስከረም 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ካለፉት ሦስት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ አዲስ መንግሥት ምስረታ እያከናወነች ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም ላይ መካሄድ የነበረበት ስድስተኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ዓለም አቀፋዊው የጤና ስጋት በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያክል ከተራዘመ በኋላ ባለፈው ሰኔ 14/2013 ዓ.ም መካሄዱን ተከትሎ ነው ዛሬ አዲስ መንግሥት እየተመሰረተ ያለው፡፡
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ እንደራሴዎች ሆነው የተመረጡት አዲሶቹ የፓርላማ አባላት ስድስተኛ ዙር የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ዛሬ ረፋድ ላይ አድርገዋል፡፡
የሁለቱን ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች እና ምክትል አፈ-ጉባኤዎችን ጨምሮ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን እንዲመሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል፡፡
ኢትዮጵያ የታሰበላትን መጥፎ አጋጣሚዎች ሁሉ በትዕግስት እና በፅናት አልፋ በዚህ ልክ አዲስ መንግሥት ስትመሰረት እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም ያሉን የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ አቶ ይህዓለም ደጉ ናቸው፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከውስጥ እና ከውጭ በተፈጠረባቸው ጫና የፈተና ጊዜያትን አሳልፈዋል ያሉት አቶ ይህዓለም “አዲሱ መንግሥት ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን ተቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን ይገባል” ነው ያሉት፡፡ የአሸባሪዎቹ ትህነግ እና ሸኔ ቡድን አባላት በተደጋጋሚ በፈጠሩት የሽብር ተግባር ዜጎች ውድ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ ሃብትና ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ወድሟል እንዲሁም በርካታ ሕዝብ ለስደት ተዳርጓል፡፡
መንግሥት ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ መፍታት ባይችል እንኳን ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሰላም ማስከበር ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል አቶ ይህዓለም፡፡
የኑሮ ውድነትን ማስታገስ እና ጠንካራ ምጣኔ ሃብት እንዲኖር መሥራት የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራ ነው ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ መጋቤ ሥርዓት አብርሃም በለጠ ናቸው፡፡ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ችግሮች ምንጭ የሆነው የሰላም እጦት ባለቤቶች የሆኑትን የሽብር ቡድን አባላት ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በከፈቱት መጠነ ሰፊ ወረራ ዜጎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ የግልና የመንግሥት ንብረት ተዘርፏል፣ ወድሟል ያሉት መጋቤ ሥርዓት አብርሃም ጦርነቱን በአጭር ጊዜ እና በማያዳግም መንገድ መቋጨት የአዲስ ተመራጩ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ፈታኝ ወቅት አዲስ መንግሥት መመስረት ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው ያለችን ደግሞ ሌላዋ የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ሰላማዊት ምህረቴ ናት፡፡ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ እና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አዲስ የተመሰረተው መንግሥት ተቀዳሚ የትኩረት መስኮች ሊሆኑ ይገባል ብላለች፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከደብረ ታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m