የኢትዮጵያ መንግሥት ምሥረታ እና ምላሽ የሚሹ የሕዝብ ጥያቄዎች።

141
ጎንደር፡ መስከረም 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ የተመሰረተው መንግሥት እንደየ ችግሮቹ አንገብጋቢነት ለዘመናት ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ ጥያቄዎችን ቅድሚያ እየሰጠ መመለስ እንደሚጠበቅበት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟትን ፈተናዎች በብቃት እየመከተች የመመለስ የረጅም ጊዜ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ አላት። ቀደም ብላ ዘመናዊ የመንግሥት አወቃቀርን የተገበረችው ኢትዮጵያ በፖለቲካ ታሪኳ ከታዩ ክፍተቶች መካከል የኢህአዴግ ዘመን ጥፋት ወደር የለውም።
አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን አድራጊ ፈጣሪ በነበረባቸው ጊዜያት በዴሞክራሲ ሽፋን በተደረጉ የይስሙላ ምርጫዎች የሕዝብ ድምጽ አልተከበረም፤ በሕዝብ የተመረጡ እንደራሴዎችም አልነበሩም። ከምርጫ ጋር በተያያዙ ችግሮች ብቻ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋልም።
የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች መሪር ግፍና በደል ደርሶባቸዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከተንኮታኮተ በኋላ ተደራራቢ ችግሮችን በመጋፈጥ እና ጫናዎችን በመቋቋም የሕዝብ ድምጽ የተከበረበት ሀገራዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቅቆ ዛሬ አዲስ መንግሥት ተመሥርቷል።
ሂደቱ ሀገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ፋና ወጊ ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚሆንም ይታመናል። ነገር ግን ወቅቱ በኢትዮጵያ እና በሕዝቦቿ ላይ ውስብስብ ችግሮች የተጋረጡ በመሆኑ አዲሱ መንግሥት ይህን መፍታት የመጀመሪያ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ቅድሚያ ሊፈቱ ይገባቸዋል ካሏቸው መካከል የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አንዱ እና አንገብጋቢው ነው። አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በተለይ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በፈጸመው ወረራ ሕዝብ ለከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግር መዳረጉ ይታወቃል። የተወረሩ አካባቢዎችን በአጭር ጊዜ ነጻ ማውጣት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ማቋቋም እና ሕዝቡን ወደ መደበኛ ሕይወቱ መመለስ የመንግሥት ተቀዳሚ የቤት ሥራ ነው ይላሉ ነዋሪዎቹ።
የጸጥታ እና የደኅንነት ስጋት ተጋላጭነት ያለባቸውን ሌሎች አካባቢዎች በጥናት ለይቶ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ነዋሪዎቹ አንስተዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፉ ሕዝብን እያማረረ ያለው የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት በአጭር ጊዜ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ነው። በሴራ የተጠለፈውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ያለውን ምርት በአግባቡ ማስተዳደር የሚቻልበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፣ ለዚህም መዋቅራዊ አሠራር ያስፈልገዋል።
አስተያዬት ሰጪዎቹ እንዳሉት በሕዝብ የተመረጡ እንደራሴዎች ሁኔታዎችን በማጥናት ለማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል። ለዚህም ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በመቋጨት እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ያለውን የጉልበት ክምችት ወደ ኢኮኖሚ መቀየር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።
የአማራ ክልል ሕዝብ ለዓመታት ያልተመለሱ ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት፣ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች አሉት። እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች አዲስ በተመሰረተው መንግሥት ፈጣን፣ ዘላቂና ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል።
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መስዋእትነት ለከፈለላቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በእኩልነት እና በነጻነት መኖር የሚቻልባት ኢትዮጵያ እውን ኾና ማየት እንደሚፈልጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሕዝቡ ላይ በተሠራ የሀሰት ትርክት የተፈጠሩ ክፍተቶችን ማስተካከል የአማራ ሕዝብ እንደራሴዎች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ዋና ጉዳይ እንደሚሆንም ተስፋ ተሰንቋል።
በፍጹም ኢትዮጵያዊ አንድነት በጋራ መኖር የሚቻልበት ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አሠራር እንዲኖር እና የአግላይ ፖለቲካዊ አካሄድ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ ማድረግ አዲሱ መንግሥት ከሕዝብ የተረከበው ኀላፊነት ነው።
ለዚህም ጫና መፍጠር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ጫና በመፍጠር ትብብር በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር አብሮ በመሥራት የአማራ ሕዝብ እንደራሴዎች የተጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
ሕዝብ ያላመነበት ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ላይ በግድ መጫኑ አሁን በሀገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን አስተያዬት ሰጪዎች አንስተዋል። ለዓመታት የቆየ የሕዝብ ጥያቄ እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበው ሕገመንግሥት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ወቅቱን በዋጀ መልኩ መሻሻል እንዳለበት አንስተዋል የሀገርን ቀጣይነት እና የሕዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥቱ ወጥ ሥርዓት ተዘርግቶለት የመጣ የሄደው እንደፈለገው ማድረግ በማይችልበት ደረጃ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላቱ ወደታች ዝቅ ብለው አስፈጻሚ አካላቱን በሚገባ መከታተልና መቆጣጠር፤ የወጡ ሕጎች በአግባቡ እየተተገበሩ መሆኑን መፈተሽ ይገባልም ነው ያሉት። የሕዝብ ጥያቄ እንዳይታፈንም መታገል ይጠበቃል ብለዋል የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች።
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ካንዣበበባት አደጋ ነጻ ሆና ኢትዮጵያዊነት የነገሰባት፣ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ለሁሉም ምቹ የሆነች የቱሪዝም ሀገር እንድትሆን ምኞት አላቸው።
በአስቸኳይ በሀገሪቱ የተከሰቱ የሰላም ችግሮች ዘላቂ ምላሽ እንዲሰጣቸው ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው። ለዚህም ፈጣን እርምጃ ያስፈልጋል ነው ያሉት። መንግሥት ያለምንም ርህራሄ ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት ብለዋል። ሕዝቡንም ለዚህ ማስተባበር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ሕዝብ ያመነበት ሕጋዊ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለበት ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በመዋቅር ውስጥ መካተት እና አዳዲስ መሪ በስፋት ወደ ፊት በማምጣት ጥሩ ውጤት እንዲመጣ አስፈላጊው ሥራ ይሠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል ።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ምክር ቤቶቹ የሕዝብ ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ የሚስተጋባበት፣ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የሚፋጩበት፣ ተከራክረው የሚያሸንፉበት ቦታ መሆን ይጠበቅባቸዋል” የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ
Next article“አዲሱ መንግሥት ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን ተቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን ይገባል” የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች