አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሀገር ሰላምና እድገት ጸር በሆኑ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ገለጹ፡፡

114

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ቻላቸው ታረቀኝ በተለይም ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ ስድስት ብሔራዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች፡፡ ያለፉት አምስት ብሔራዊ ምርጫዎች በየአምስት ዓመት ዘመኑ ወይም ጊዜአቸውን ጠብቀው ከመካሄዳቸው በስተቀር ምርጫ ተካሂዷል ለማለት እንኳ አያስደፍርም ባይ ናቸው፡፡ ዲሞክራሲያዊ መስፈርቱን ያሟሉ እንዳልነበሩ በማንሳት፡፡

በአንጻሩ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሻለ መልኩ ዲሞክራሲያዊ እንደነበር አንስተው በኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት ላይ ተስፋ መፈንጠቁን አስረድተዋል፡፡

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሻለ ስኬት አከናውና ነገ መስከረም 24/2014 ዓ.ም መንግሥት የምትመሰርተው ኢትዮጵያ እዚህ ለመድረስ የነበሩ ፈተናዎችን መምህር ቻላቸው አንስተዋል፡፡

የመጀመሪያው እና ዋናው ፈተና እና እንቅፋት ብለው የጠቀሱት ከለውጡ አፈንግጦ የወጣው ሽብርተኛው ትህነግን ነው፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ሽብርተኛው ትህነግ በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፤ ከሽብርተኛው ሸኔ፣ ከጽንፈኛው የቅማንት ታጣቂ ቡድን እና ከጉሙዝ ታጣቂዎች ጋር በመሆን ዜጎችን ገድለዋል፣ አፈናቅለዋል፣ ዘርፈዋል፤ አውድመዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት ሀገር የማተራመስ እና የማፍረስ ሴራውን እውን ለማድረግ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዛም በኋላ ሸብተኛው ትህነግ የአማራን እና የአፋር ክልሎችን በመውረር መጠነ ሰፊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ነው ምሁሩ የገለጹት፡፡

መምህር ቻላቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ምክንያት የዋዠቀ አቋም የሚያንጸባርቁት ግብጽ እና ሱዳን፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሽብርተኛው ትህነግ ደጋፊ ምዕራባውያን ጫና እና ዳረጎት ሲቆርስላቸው የነበሩ የውጭ ብዙኃን መገናኛ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት መሥረታ ላይ የነበራቸው ጫና ቀላል እንዳልነበር ነው የጠቀሱት፡፡

እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ሳይበግሩት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መደረጉ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት በስኬት ተከናውኖ ሽብርተኛው ትህነግም ላይ እርምጃ እየተወሰደ ኢትዮጵያ ነገ መስከረም 24/2014 ዓ.ም ለመንግሥት መሥረታ መብቃቷ ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን መምህሩ ገልጸዋል፡፡

ነገ መስከረም 24/2014 ዓ.ም የሚመሠረተው መንግሥት የሚጠብቁት ዋና ዋና የቤት ሥራዎች ብለው መምህር ቻላቸው ከጠቀሷቸው ውስጥ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ እና ሃብትና ንብረታቸውን የመጠበቅ ኀላፊነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም ሽብርተኛው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ያደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ያነሱት ምሁሩ በአማራ ክልል አሁንም ድረስ ዜጎች በመከራ ውስጥ እንደሚገኙ በማንሳት መንግሥት ይህን በአጭር ጊዜ መፍታት አለበት ነው ያሉት፡፡

የመንግሥት መሥረታው ዋና ዓላማ ዜጎችን ከሰብዓዊ ጥቃት መታደግ እና ንብረታቸውን ከውድመት እና ከዘረፋ መጠበቅ መሆኑን ከታሪካዊ ዳራው የጠቀሱት መምህር ቻላቸው ነገ የሚመሰረተው የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን ዓብይ ዓላማ በብቃት እና በአጭር ጊዜ ሊወጣ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

መምህር ቻላቸው መንግሥት በሽብርተኛው ትህነግ፣ በጽንፈኛው የቅማንት ታጣቂ ቡድን፣ በሽብርተኛው ኦነግ ሸኔ እና በጉሙዝ ታጣቂ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ ግድ ይለዋል ብለዋል፡፡

ሌላው ነገ የሚመሠረተው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፣ የታሪክ ሥርዓተ ትምህርቱን ማሻሻል እና መሰል የሚነሱ ተቃርኖዎችን ዘላቂ እና የዜጎችን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ማስታረቅ እንዳለበት መምህር ቻላቸው ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ዜጎችን እያስጨነቀ መሆኑን ያነሱት መምህሩ የኢኮኖሚ አሻጥሩን በማክሸፍ ረገድ ሌላው መንግሥት የሚጠብው ወሳኝ የቤት ሥራ መሆኑን መምህር ቻላቸው አንስተዋል፡፡

መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማሻሻል፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ሕይወት መቀየር እና መሠል ኀላፊነቱን በአግባቡ መፈጸም እንደሚጠበቅበትም አስረድተዋል፡፡

አሁን ያሉባትን ጫናዎች መቋቋም የምትችል ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ውስጣዊ አንድነት ወሣኝ መሆኑን ያነሱት መምህሩ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ለነገ የማይባል ሥራ መሆን አንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሚሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በቁርጠኝነት በመውሰድ የሽብርተኛውን ትህነግ ኃይል ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውን የብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ሰልጣኞች ገለጹ።
Next articleየቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ አባሳንጆ ኢትዮጵያ በምትመሰርተው መንግሥት ለመታደም አዲስ አበባ ገቡ።