
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ መልኩ ዲሞክራሲያዊ ነው የተባለለትን ምርጫ ካደረገች በኋላ አዲስ መንግሥት እያወቃረች ነው። ለኢትዮጵያ ደግ የማይመኙ እና የኢትዮጵያውያን መከራ ማዬት የሚናፍቃቸው ጠላቶች ኢትዮጵያ ምርጫ ልታካሂድ አትችልም ብለው ነበር። ኢትዮጵያ ግን ሰላማዊ ምርጫ አካሂዳ አሳይታለች። የተባለችው ቀርቶ ያሰበችው ኾኗል። ኢትዮጵያ ምርጫ ካደረገችበት ማግሥት እና አሸናፊው ከታወቀ በኋላ አዲስ መንግሥት ምሥረታ ላይ ትገኛለች።
የፌዴራል መንግሥቱ አዲስ መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ክልሎች መንግሥታቸውን እየመሠረቱ ነው፤ መሥርተዋልም። በፈተናዎች ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልልም በአንድ በኩል የገጠመውን ፈተና እየመከተ በሌላ በኩል አዲስ መንግሥት መሥርቷል።
በተመሰረተው አዲስ የክልል መንግሥትም አዲስ ርእሰ መሥተዳድር፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና ሌሎች አዳዲስ ሹመቶች ታይተዋል።
በተመሠረተው አዲስ መንግሥትም ሕዝብ ተስፋ ጥሏል። አሸባሪውና ወራሪውን የትህነግ ቡድን ከክልሉ ብሎም ከሀገሪቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ መጣል፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋምና ወደ ቀደመ ሕይዎት መመለስ፣ የተቋረጡ ልማቶችን ማስቀጠልና ሌሎች ታላላቅ ጥያቄዎች ይመለሱ ሰንድ ሕዝብ በአዲሱ መንግሥት ተስፋ የጣለባቸው ጉዳዮች ናቸው። አዲሱ መንግሥትስ ምን ይመልስ ይሆን?
በአዲሱ የመንግሥት አወቃቀር የአማራ ክልል ርእሰ መሥተደድር ኾነው የተሾሙት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲሱ መሪ ራሱን ለመስዋእት ያዘጋጀ ነው፣ ሕዝብን ከመከራ እናወጣለን፣ የሰላም አየር መተንፈስ አለበት ብሎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። መሪዎቹ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
❝እኛ ግቡን እንድናሳካ ከተፈለገ መላው ሕዝብ በየደረጃው ከሚገኝ መሪ ጎን በመሰለፍ፣ የሚፈለግበትን አስተዋጽኦ ያለ ምንም መጠራጠር፣ ያለምንም ይሉኝታ መሪውን መደገፍ ይገባዋል❞ ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ እየተገደለና እየተፈናቀለ መሆኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝብና መንግሥት የገነባው መሠረተ ልማት እየወደመ ነውም ብለዋል። በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል አዲስ ለመጣው መሪም ሆነ ለአማራ ሕዝብ የእግር እሳት መሆኑን ገልጸዋል። አዲስ የመጣው መሪም ውስብስቡን ችግር የተረዳ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲሱ መንግሥት ቁልፍ ጉዳይ ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ ፣ የተወረሩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን እና ወገኖችን ከጠላት ነፃ ማድረግ ቁልፉ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት በንግዱ ማኅበረሰብ የሚታዩ ክፍተቶችን እንደሚከታተልም አመላክተዋል።
የአማራ ሕዝብ የሚሸነፍ፣ የሚከፋፈልና የሚበታተን ሕዝብ ሳይሆን ጠላት በመጣበት ጊዜ ቀፎው እንደተነካ ንብ “ሆ” ብሎ በአንድነት እንደሚወጣ በትክክል ያሳዬ ነውም ብለዋል።
ጠላት ከክልሉ አልወጣም ያሉት ዶክተር ይልቃል የተጀመረውን ጅምር ሁሉ አንድ በመሆን ትግሉን ማጠናከር ድሉን ስለሚያፋጥን በዚህ መንፈስ መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m