
መስከረም 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1949 በጄኔቫ የወጣውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል የወጣውን ኮንቬንሽን ስምምነት ፈራሚ ሀገር ናት። ሀገሪቱ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 ላይ አንድን ብሔር በብሔርነቱ ወይንም በሃይማኖቱ መሰረት ተደርጎ ዘሩ እንዳይቀጥል ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን እንደሚደነግግ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዲን እና መምህር ሰለሞን ጎራው ገልጸዋል።
ታዲያ አሸባሪው ትህነግ ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በመጣስ ከምስረታው ጀምሮ አማራን በጠላትነት በመፈረጅ እንደ ብሔር ዒላማ አድርጎ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን መምህሩ ተናግረዋል።
አሸባሪው ትህነግ ከስልጣን ከተባረረ በኋላም በጦርነት ስልጣን መልሶ ለመቆጣጠር ያደረገው ወረራ ራሱ ያወጣውን ሕገ መንግሥት ጭምር የጣሰ እና ወንጀለኝነቱን ያረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል። በከፈተው ወረራም በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦርነት ሂደት፣ የንጹሐን ዜጎች፣ ንብረቶቻቸው እና የሃይማኖት ተቋማት እንዳይነኩ የሚከለክለውን ድንጋጌ ሙሉ በሙሉ በመጣስ ስለ ፈጸማቸው ግፎች በቂ ማስረጃዎች መውጣታቸውን እና እየወጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
መምህሩ እንዳብራሩት ሽብርተኛው ትህነግ በጦርነት ዒላማ መሆን የማይገባቸው ንጹሐን ዜጎችን በአጋምሳ፣ በማይካድራ፣ በጭና፣ ቆቦ፣ ጋሊኮማ እና ሌሎችም አካባቢዎች ሆን ብሎ ወይንም ያለልዩነት ገድሏል፤ ታሪካዊ ቅርሶችን እና የሃይማኖት ተቋማትን በማውደም የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል።
መምህር ሰለሞን መንግሥት የጽሑፍ ማስረጃዎችን በመሰነድ፣ የሰው ምስክሮችን በማሰማት እና አካላዊ ማስረጃዎችን ጭምር በማቅረብ ሽብርተኛው ትህነግን በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳለበት ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲዎችና የፍትሕ ተቋማት ሽብርተኛው ትህነግ የፈጸማቸውን ወንጀሎች በጥልቀት በማጥናት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ማሳወቅ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ሽብርተኛው ትህነግ ለጦርነት ያልደረሱ ሕጻናትን በመመልመልና በጦርነት በማሰለፍ ሀገሪቱ የፈረመችውን ዓለም አቀፍ ሕግ በመጣስ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ስለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ነው ብለዋል ።
ሽብርተኛው ትህነግ በሌሎች ክልሎች በንጹሐን ላይ በፈጸመው ወንጀል እና የራሱን ዜጎችም ያለአግባብ የጦር መጠቀሚያ በማድረግ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ እንደሆነ አንስተዋል። ድርጊቱ በቀጣይ በኢትዮጵያ እንዳይደገም መንግሥት እና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m