
መስከረም 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ታሪክ ይቅር የማይለው በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አድርሷል፡፡ በርካቶች ለሞት፣ ሕጻናት ለእንግልት፣ ዜጎች ለስደት፣ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ለከፋ መከራ ተጋልጠዋል፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን ነፃ በወጡ የክልሉ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያረጋገጠውም በንጹሐን ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ እና የሥነ ልቦና ስብራቶችን ነው፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ደብረ ዘቢጥ ከተማ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በከባድ መሳሪያ ታግዞ በከፈተው ጦርነት ዜጎች ሕይወታቸውን ብሎም ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡
ቄስ አከለ ታረቀኝ በሰሜን ወሎ ዞን ደብረ ዘቢጥ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ84 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከተማዋን በወረረበት ወቅት በርካታ መኖሪያ ቤቶችን ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯቸዋል ይላሉ፡፡
“የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ወደ ፈረሰው ቤት ዘልቀው ሲገቡ ጣራ እና ጥቀርሻ ተጭኖን ከአልጋ ላይ ያገኙን እኔን እና ባለቤቴን ነው” ያሉት ቄስ አከለ ለዕለት የበሰለ ምግብ እንኳን ሳይተው እንደዘረፏቸው ነግረውናል፡፡
“አቅመ ደካማ ሽማግሌ ነኝ፤ መሸሽ አልችልም ወደ ቤቴ አትዝለቁ ስለመድኃኔዓለም ብዬ በተደጋጋሚ ለምኛቸዋለሁ” ያሉት ቄስ አከለ ሽማግሌን ‘ተልዕኮ አለህ’ እያሉ ማንገላታት በዘመኔ አይቼ አላውቅም” ነው ያሉት፡፡
በከባድ መሳሪያ ከፈረሰው ቤታቸው ላይ ላስቲክ ዘርግተው ዝናብ፣ ፀሐይ እና ብርድ የሚፈራረቅባቸው ቄስ አከለ ቤቱ ላይ ያረፈው ፍንጥርጣሪ ታፋቸው ላይ ጉዳት አድርሶ ለሕመም እንደተጋለጡም ነግረውናል፡፡
ሌሎች የከተማዋ ነዋሪ አቅመ ደካሞቹ አቶ አስናቀው አሰፋ እና ወይዘሮ ብዙየ ታረቀኝ ከእሁድ እስከ ሐሙስ በከባድ መሳሪያ ከተመታ ቤታቸው ፍርስራሽ ስር የመከራ ቀናትን አሳልፈዋል፡፡ አቶ አስናቀው የመስማት ችግር ሲኖርባቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ብዙየ ደግሞ ዓይነ ስውር ናቸው፡፡ በፍርስራሽ ቤታቸው ጣራ ስር አምስት ተከታታይ ቀንና ሌሊትን ያሳለፉት ጥንዶቹ ሞተዋል ተብለው ስለተረሱ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት እንኳ ወደ ቤታቸው ፍርስራሽ አላመሩም ነበር፡፡
“የምንጠጣው ውኃ አጥተን ላስቲክ ላይ የቋተ የዝናብ ውኃ ለባለቤቴ አጠጥቻታለሁ” ነው ያሉት አቶ አስናቀው፡፡
ከተማዋ ከሽብር ብድኑ ነፃ ከወጣች በኋላ ወደ ቀያቸው የተመለሱ የአካባቢው ሰዎች እና የጸጥታ ኃይሉ ምግብ በማቅረብ ከሞት እንደታደጓቸው ነግረውናል፡፡
የዕለት እርዳታ ከወገን እና ከመንግሥት እንደቀረበላቸው የገለጹት ጥንዶቹ የቤታቸው መፍረስ ምግብ አብስሎ ለመጠቀም እንኳን እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ ቄስ አከለ እና አቶ አስናቀው በከተማዋ በርካታ ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረው ዜጎች ዛሬም የመከራ ቀን እና የስቃይ ሌሊትን እንዲገፉ ግድ ብሏቸዋል፡፡
ቤት አልባ ባለቤቶቹ ማኅበራት፣ መንግሥት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች “ከላያችን ላይ የተከፈተውን ሰማይ እንዲከልሉልን እንማጸናለን” ነው ያሉት፡፡
በአካባቢው በከፍተኛ ወጭ የተሠሩት የኤሌክትሪክ መስመሮች ተበጣጥሰዋል፤ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ዜጎች ለበርካታ ዓመታት ሃብታቸውን እና ጉልበታቸውን ያፈሰሱባቸው ረጃጅም እና ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ የነበራቸው የባሕር ዛፍ ተክሎች ጭምር የከባድ መሳሪያ አረር ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በአካባቢው የደረሰው ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ቁሳዊ ውድመት የከፋ ቢሆንም መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ ግን ከሁሉም የከፋ መሆኑን አስተውለናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከደብረ ዘቢጥ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m