የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለኦሮሞ ሕዝብ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ።

195

የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈው ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከኦሮሞ ህዝብ የፍቅር፣ የወንድማማችነትና የሰላም ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል አንዱ ለሆነው የኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ እያለ በዓሉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ያጠላው የክፋት ደመና በአንድነታችን ተገፎ ለሀገራችን ብሩኅ የብልጽግና ዘመን የምናመጣበት እንዲሆን ይመኛል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ያበረከተው አንዱ የባህል እሴታችን እንደመሆኑ ሁላችንም በደስታ የምንቀበለው በዓል ነው፡፡ የበዓሉ እሴቶች የሆኑት ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርና ወንድማማችነትም አንድነታችንን የምናሳድግባቸው ጽኑ የኢትዮጵያዊ አሸናፊነት ምስጢራት ናቸው፡፡

በዓሉ ከኢትዮጵያ ጠላቶችና የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ተጻራሪ ከሆኑ ኃይሎች ጋር ተሰልፎ ህዝባችንን ለማንበርከክ እየሠራ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን በምንፋለምበት ወቅት የሚከበር እንደመሆኑ በጠላቶቻችን ላይ ያለንን ከዐለት የጠነከረ አንድነት የምናሳይበትም ጭምር ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ይህንን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የተሰለፈ ጠላት ለመፋለም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በአማራና በአፋር የተለያዩ የጦር ግንባሮች ሀብቱን እንዲሁም ልጆቹን በመላክ ዛሬም እንደ ጥንቱ ለሀገራችን አንድነት በመዋደቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ከድንቅ ባህላዊ እሴቶቹ የሚቀዳ በደም የተከተበ የወንድማማችነት እሴት ማሳያ በመሆኑ የኢሬቻ በዓል ሲከበርም እየተስተዋለ የሚገኝ ግዙፍ ሀቅ ነው፡፡

ይህ የአንድነታችን ማሳያ የሆነው የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት እለትም የአማራ ክልል መንግሥት የኦሮሞ ህዝብ ለጸጥታ ኃይሉ ከሚያቀርበው ኃብት በተጨማሪ የኦሮሞ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል የአማራ ህዝብ በአሸባሪውና በወራሪው ኃይል የደረሰበትን በደል በመከላከል ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ለሚያደርገው ተጋድሎ ሁሉ የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

የከበደው የክረምት ወቅት አልፎ ምድር ከከበደው ክረምት በምታገኘው የእጽዋት ልምላሜና ስነ አበባ እንደምትዋበው ሁሉ ኢትዮጵያውያንም በአንድነታችንና ጽኑ ኅብረታችን የገጠመንን ፈተና በድል ተሻግረን ለአማረውና ለተዋበው ብልጽግናችን እንደምንደርስ ሙሉ እምነት አለን፡፡

ኢሬቻ መጪዉ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ቃል የምንገባበት በዓል እንደመሆኑ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ዛሬም እንደ ትላንቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን የእናት ጡት ነካሽ እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ልክ በማስገባት ለሁላችንም የተመቸች የውዲቷን ኢትዮጵያ ትንሳኤ እንደምናበስር ሙሉ እምነት አለን፡፡

መልካም የኢሬቻ በዓል ይሁንልን!

Previous article“በአዲስ አበባ የተከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ካለፉት አመታት አንፃር በደማቅ ስነ-ስርአት ተከናውኗል” ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
Next articleበአማራ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመመከት የተጀመሩ ሁሉ አቀፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።