“በአዲስ አበባ የተከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ካለፉት አመታት አንፃር በደማቅ ስነ-ስርአት ተከናውኗል” ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

187
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ የተከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ካለፉት ዓመታት አንፃር በደማቅ ሥነ-ስርዓት መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባዋ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ እየተከበረ የሚገኘው የኢሬቻ በአል ባለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ መምጣቱን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አንስተዋል።
በመዲናዋ በዓሉ ሳምንቱን ሙሉ በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች ሲከበር እንደነበርም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ሕዝብ የኦሮሞ ወገኖቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ያሳየው ድጋፍ እና ፍቅር በመልካም ምሳሌነቱ የሚነገርለት ነው ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።
ከንቲባዋ የሕዝቦች አንድነት የበለጠ መጠናከሩን የገለፁ ሲሆን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲጎለብትም በዓሉ ድርሻው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የአሸባሪው የህውሃት ቅጥረኛ የሆነው ሸኔ ያሰማራቸው የተወሰኑ የጥፋት ኀይሎች በዓሉን ሊረብሹ ሙከራ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
እነዚህ አካላት ሌሎች ጥፋቶችን ለመፈፀም ያቀዱ ቢሆንም የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት በአዲስ አበባ አምስቱም በሮች ፍተሻና ጥበቃ በማድረጋቸው ያሰቡት ሴራ መክሸፉንም ተናግረዋል።
በዓሉ በሰላም በመጠናቀቁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ላይ የታየው ጨዋነት በነገው እለትም በቢሾፍቱ እንዲደገም ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቅርበዋል። ዘገባው የኢብኮ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየደቡብ ወሎ ሕዝብ የአሸባሪውን ትህነግ ወረራ ለመመከት በተደራጀ መንገድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡
Next articleየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለኦሮሞ ሕዝብ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ።