የደቡብ ወሎ ሕዝብ የአሸባሪውን ትህነግ ወረራ ለመመከት በተደራጀ መንገድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡

127
ደሴ፡ መስከረም 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ሕዝብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተንቀሳቀሰውን የትህነግ አሸባሪ ቡድን ባለበት እንዲደመሰስ የሚችለውን እያደረገ እንደሆነ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ሰይድ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰይድ አሸባሪው ቡድን ሕፃናትን፣ ነፍሰጡሮችን እና ሽማግሌዎችን አስከትሎ በአማራ ክልል ወረራ ፈጽሟል፤ በዚህም ብዙ ንጹሃን ላይ በደል አድርሷል ነው ያሉት፡፡
ጦርነቱ እንደተከፈተ ዞኑ በተደራጀ መንገድ የደረሰበትን ግፍ ለመመከት ዝግጅት አልነበረውም ያሉት አቶ ሰይድ ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የደረሰውን ውድመት የተገነዘበው ሕዝብ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በመኾን ዘግይቶም ቢሆን በተደራጀ መንገድ አጥፊው ቡድን ባለበት እንዲደመሰስ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሕዝብ የጋራ አቋም በመውሰድ ማንም አካባቢውን ጥሎ መሸሸ እንደሌለበት በመወሰን ወደ ትግሉ ተገብቷል ብለዋል፡፡ የተሠራው የግንዛቤ ፈጠራ ተጨማሪ ዜጎች እንዳይፈናቀሉ ማስቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በደቡብ ወሎ በአራቱም ግንባሮች ማለትም በወረባቦ፣ በተሁለደሬ፣ በውጫሌ እና በደላንታ ከአንድ ወር በላይ ጦርነት ተካሂዷል ያሉት አቶ ሰይድ ሕዝቡ ለጸጥታ አካላት የሰጠመው ምላሽ ወራሪው ቡድን አሁን ባለበት እንዲገታ እንዳስገደደው ጠቁመዋል፡፡
ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር ተሰልፎ የፈጸመው ጀብድም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ቀድሞ በወረራቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ወደ ደሴ፣ ኮምቦልቻና አካባቢው መፈናቀላቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መፈናቀሉን ነው የተናገሩት፡፡ ለተፈናቃዮች የተለያዩ ዞኖች በሚችሉት ልክ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት በአጭርና በረጀም ጊዜ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ግብረ ኀይል በማቋቋም እየሠራ ነው ያሉት አቶ ሰይድ ሥራው ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል፡፡
ድጋፉም የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋምና ወራሪው ቡድን ድጋሜ ለሀገር ሥጋት በማይኾንበት መልኩ በአጭር ጊዜ ማጥፋት ሊኾን እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ ማጥፋት ካልተቻለ የሚፈናቀሉና የሚሞቱ ንጹሃን ቁጥር መጨመሩ አይቀርም፤ ይህ እንዳይሆን በሀገረ ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሊደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ጦርነቱን በአጭረ ጊዜ ለማሸነፍ የተሟላ ዝግጅት ማድረግና መወሰን ይጠበቃል፤ ውሳኔውን ለማስተግበር ደግሞ ግብዓት ማቅርብና ጠላትን በሚገባ ቋንቋ ማናገር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
Next article“በአዲስ አበባ የተከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ካለፉት አመታት አንፃር በደማቅ ስነ-ስርአት ተከናውኗል” ወይዘሮ አዳነች አቤቤ