“አዲሱ የክልሉ መንግሥት መዋቅር የአማራን ሕዝብ ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ እንዲሠራ ያስችለዋል” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ

373
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መስከረም 20/2014 ዓ.ም አዲስ መንግሥት መስርቷል። አዲስ የተመሠረተውን የክልሉን መንግሥት አስመልክቶ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ማብራሪያውን የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በአዲስ መልኩ የተዋቀረው የክልሉ ካቢኔ የክልሉን ሕዝብ ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። 75 በመቶ በአዲስ የተተኩት የአማራ ክልል የሥራ ኀላፊዎች በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በዕድሜያቸውም ኾነ በሥነ ምግባራቸው ብቁ በመሆናቸው ክልሉ የገጠመውን ዘርፈ ብዙ ችግር ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
አዲሶቹ ተሿሚዎች የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን አደጋ የመቀልበስና የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል እውቀት እና ችሎታ ያላቸው መሆናቸውን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።
በአዲስ የተዋቀሩ ተቋማትም ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎችን አቅደው ይሠራሉ ነው ያሉት። ከአዲሱ የመንግሥት ምስረታ ጎን ለጎን የአማራ ክልል ሕዝብ የገጠመውን የህልውና አደጋ ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ ውይይት መደረጉን ኀላፊው ጠቁመዋል። ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት የአማራ ሕዝብ ሰቆቃ፣ እንግልትና መፈናቀል እንዲያበቃ እንደሚሰሩ የገለጹበት መሆኑንም አቶ ግዛቸው አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ የደኅንነት ጉዳይ ሁልጊዜ ቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን በምክር ቤቱ አቅጣጫ መቀመጡንም ኀላፊው አስረድተዋል።
በአሸባሪው የትህነግ ቡድን የተወረሩ አካባቢዎች በፍጥነት ነፃ በሚወጡበት ሁኔታ ላይ ከጸጥታ አካላት፣ ከፌዴራል መንግሥትና ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን አስፈፃሚው አካል በቅርበት እንዲሠራ፣ ውሳኔዎችም እንዲወሰኑ እና ለሁሉም ተግባር ኀላፊነት ወስዶ ክልሉ እንዲሰራ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን አመላክተዋል።
በወረራ ሥርም ኾነ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ዋነኛ ተግባር እንዲኾንም ተወስኗል ብለዋል።
የተዘረፉና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከውስጥም ኾነ ከውጪ ሠፊ የሀብት የማሰባሰብ ተግባር እንዲከናወን በምክር ቤቱ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ ግዛቸው ጠቁመዋል። የሚደረገው ድጋፍም ወደ አንድ የድጋፍ ማእከል ገብቶ እንዲሰበሰብና ለተጎጂዎች እንዲደረስ አቋም መያዙንም ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት።
ለተፈናቃይ ወገኖች እየተደረገ ያለውን የመረዳዳት ባሕል በማሳደግ እርስ በርስ መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። የውጪ ድጋፍ እስኪገኝ የዜጎች ችግር በዝምታ እንደማይታይም ጠቁመዋል።
በተለይ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን በደል በተጨባጭ መረጃ ማስረዳትና ማጋለጥ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የሚደረገው ትግል ሕጋዊና ለነፃነት እንደሆነ ለዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ማስረዳት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ከህልውናው ዘመቻ ጋር ተያይዞ ራስን የማደራጀት፣ የማብቃት፣ በወታደራዊም ሆነ በሎጅስቲክ ራስን በማጠናከር ከጠላት ነፃ ለመሆን መሠራት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት ዋነኛ ተግባር አድርገው መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
ሀገርን ለማፍረስ አቅዶ እየሠራ የሚገኘውን አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ለማጥፋት የአማራ ክልል መንግሥት ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በተቀናጀ መልኩ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ቡድኑን ለማጥፋት አስፈላጊውን የሰው ኀይል ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊትና ወደ አማራ ልዩ ኀይል በማካተት መሰራቱንም አስገንዝበዋል።
ከመደበኛ የጸጥታ መዋቅሩ በተጨማሪም የየአካባቢው ማኅበረሰብ ጠላት የረገጠው መሬት ሁሉ እሾህ እንዲሆንበት የቤት ሥራ ወስደው እየተገበሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ እንዳይፈናቀል አዲሱ የክልሉ መንግሥት ከጎረቤት ክልሎችም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀራረብ የሕዝብን አጀንዳ ለይቶ ይሠራልም ብለዋል።
“አዲሱ የክልሉ መንግሥት መዋቅር የአማራን ሕዝብ ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ እንዲሠራ ያስችለዋል” ብለዋል። ሁሉም የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሕጋዊ መልኩ የሚመለሱ እንደሆኑ አቶ ግዛቸው አስገንዝበዋል። የሕዝቡ ጥያቄ በየደረጃው የሚፈታ እንደኾነም ኀላፊው አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአዋሽ ቢሾላ ማሰልጠኛ ማእከል ለኹለተኛ ዙር ምልምል ሰልጣኞች የስልጠና ማስጀመሪያ ተከናወነ፡፡
Next articleየኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡