
ደሴ፡ መስከረም 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በሰላም ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በማኅበር እንደመጡ የነገሩን ወይዘሮ የሸዋገር ዘለቀ እንዳሉት የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ድባብ ለማደብዘዝ በማኅበራዊ ሚዲያ የተነዛውን አሉባልታ ባለመቀበላቸው ከቦታው ተገኝተው ያለምንም ችግር በዓሉን ማክበራቸውን ነው የነገሩን። የአካባቢው ማኅበረሰብ አቀባበልም የቆየውን እንግዳ አክባሪነት ያሳየ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሌላኛዋ ከሸኖ እንደመጡ የነገሩን ጀማነሽ ይስሜ በቦታው ተገኝተው በዓሉን ለአራተኛ ጊዜ እንዳከበሩት ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ከመስከረም15/2014 ዓ.ም ጀምረው በዓሉን ለማክበር እንደተገኙ ገልጸዋል።
በዓሉ ደምቆ እንዳይከበር በማኅበራዊ ሚዲያ አሉባልታ ሲናፈስ መቆየቱን ተናግረው ወሬው ግን እንዳልገደባቸው ነው ለአሚኮ ያስረዱት። ማኅበራዊ ሚዲያን አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው ታቅበው ለሀገር ግንባታ እንዲያውሉት መክረዋል።
ከአዲስ አበባ እንደመጡ የነገሩን ቢኒያም ስንታየሁ ደግሞ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የግሽን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓልን በማኅበር ሆነው በስፍራው በመገኘት አክብረዋል። በዚህ ዓመትም 15 ሆነው አክብረዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ሲናፈስ ለነበረው አሉባልታ ጆሮ ባለመስጠት ከመሥከረም 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ከቦታው ተገኝተው በዓሉን በሰላማዊ መንገድ አክብረዋል።
በግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል ወጣቶችና የጸጥታ አካላት በቅንጂት ሰላም በማስከበር ኀላፊነታቸውን እንደተወጡም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር የወጣቶች እና የጸጥታ መዋቅሩ በመቀናጀት በየቦታው ሲደረግ የነበረው ጥበቃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል። በየአካባቢው ለተደረገላቸው አቀባበልም አመስግነዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ-ከግሽን ደብረ ከርቤ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ