
አዲስ አበባ፡ መስከረም 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 76ኛው ጉባዔ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን መሪነት የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከመደበኛ ስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ልዑካን ጋር ውይይቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል። ውይይቶቹም የተመረጡና ለኢትዮጵያ ወቅታዊ አጀንዳ አስፈላጊነታቸው የተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱም አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ወረራ፣ እየተደረገ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ፣ ስለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር እና መሰል እውነታዎች እና አቋም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘቧን ገልጸዋል፡፡
ከመንግሥታቱ ድርጅት ዋና እና ምክትል ጸሐፊዎችና ሌሎች መሪዎች ጋርም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ በኮሮና ቫይረስ ፈተናዎች፣ በአየር ንብረት ለውጥና በዋናነት ደግሞ በሀገራት መካከል መኖር ስላለበት የግዛት አንድነትና የፖለቲካ ነፃነትን ያከበረ ግንኙነት አንስተዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የሰላም ሥራዎችን፣ የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያን አቋም የሚገልፅ ንግግር አካሄደዋልም ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፣የኡጋንዳ፣ እንግሊዝና የተለያዩ ሀገራት ያሉ የኢትዮጵያ አምባሰደሮችም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳዩች የሚያስረዱና የሀገራትን ግንኙነትን የሚያሳድጉ ውይይቶችን ከየተወከሉበት ሀገራት የሥራ ኀላፊዎች ጋር መካሄዱንም ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴሩ እያካሄደ ለሚገኘው ተቋማዊ ለውጥ የሚያግዙ ስልጠናዎችን መስጠቱንም ገልጸዋል።
በሳምንቱ ከአልጀሪያ፣ ባህሬንና ህንድ ሀገራት ጋር የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተከናውነዋል።
በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ላይ ያሉ ጫናዎችን በመቃወምና በተለያዩ ዘርፎች ለሀገራቸው ድጋፍ ያደረጉበት ሳምንት ነበርም ብለዋል። ከተለያዩ ሀገራት ዜጎችን የመመለስ ሥራዎች አሁንም መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ