“ሕዝብን ለማገልገል መመረጥ ትልቅ እድል ነው” የአማራ ክልል የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ

517
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛ መሥራች ጉባኤውን እየካሄደ የሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን አፈጉባኤ አድርጎ መርጦ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ በጉባኤው ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ “ሕዝብን ለማገልገል መመረጥ ትልቅ እድል ነው” ብለዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላሳየው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥጋና ችረዋል። ምክር ቤቱም ሕገ መንግሥትን መሠረት በማድረግ የተጣለበትን ኀላፊነት በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ይወጣል ነው ያሉት። በተለይ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ከምርጫ ማግስት የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ አማራን እና አፋርን በመውረር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተው የጸጥታ ኃይሉ እና ሕዝቡም ወረራውን ለመቀልበስ መስዋእትነት እየከፈለ ነው ብለዋል። ምክር ቤቱም በክልሉ እና በሀገር ያንዣበበውን አደጋ ለመመከት መከላከያን፣ ልዩ ኃልን፣ ሚሊሻን እና ፋኖን በመደገፍ በቀጣይ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሀገር ውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለህልውና ዘመቻው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አፈጉባኤዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው
Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር መስራች ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ።
Next articleቢጄአይ ኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።