
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 7ኛ ዓመት 18ኛ መጨረሻ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡ ምክር ቤቱ የክልሉን የ2014 በጀት 80 ቢሊየን 104 ሚሊየን 669 ሺህ 397 ብር እንዲሆን አጽድቋል።
የአማራ ክልል በአሸባሪው ትህነግ በተከፈተበት ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቀው ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል። በመሆኑም ክልሉ በሚያመነጨው ልክ ገቢ መሰብሰብ አለበት ብለዋል። መሪዎችም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ከታቀደው በላይ ገቢ እንዲሰበሰብ መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
አቶ አገኘሁ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ወረራ ቢፈጽምም ወረራውን ለመመከት የክልሉ ሕዝብ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች ያደረጉት ተሣትፎ እጅግ የሚደነቅ ነው ብለዋል፤ ምስጋናም አቅርበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት ለህልውና ዘመቻው ከንግዱ ማኅበረሰብ የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ እየተደረገ ነው፤ አርሶ አደሮችም ጥሩ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፤ ይህንንም አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኅብረሰብ ክፍሎችም ለህልውና ዘመቻው በታሪክ ከፍ ብሎ የሚመዘገብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ አገኘሁ አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥልጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አገኘሁ እንደገለጹት ሽብርተኛው ትህነግ በፈጸመው ወረራ ምክንያት በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በተለይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ማቋቋም ካልተቻለ ለተማሪዎች ትምህርት መስጠት አይቻልም ብለዋል። ይህ ደግሞ በክልሉ ሃብት ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ቀርቧል፤ ክልሎችም ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አገኘሁ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችም በቦታው ተገኝተው ጉዳቱን እየተመለከቱ መሆናቸውን ጠቅሰው በቂ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ❝ጦርነቱን ለመመከት መንግሥት እየሠራ ነው፤ ከጦርነት በኋላ ግን ሕዝባችንን መልሰን ማቋቋም ይገባናል❞ ብለዋል፡፡ ለዚህም ክልሉ በአሁኑ ወቅት የልዩ ኃይልንና መከላከያ ሠራዊትን ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቀጣይ ሕዝብን መልሶ ከሟቋቋም በላይ ሥራ አይኖርም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ጸጥታ መዋቅርም እየሠራ ለሚገኘው ጠንካራ ሥራ ምስጋና ችረዋል።
በዚህ ወቅት ከሽብርተኛው ትህነግ ባልተናነሰ መንገድ ያለ አግባብ ዋጋ በሚጨምሩ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይም ትኩረት ተሰጥቶ የማስተካከል ሥራ እንደሚሠራ አቶ አገኘሁ ጠቁመዋል፡፡ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል። ሁሉም መሥሪያ ቤቶች የተመደበውን በጀት ተገቢ ባልሆነ ወጪ ከማባከን ተቆጥበው በጥንቃቄ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ