
ደሴ፡ መስከረም 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገሪቱ ከውስጥ እና ከውጭ የተደቀነባትን አደጋ ለመመከት ሕዝባዊ አንድነትን ማጠናከር ከአዲሱ መንግሥት እንደሚጠበቅ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ካሳ አሊ እንዳሉት አዲሱ የሚመሰረተው መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ ይገባል። “ለሕዝብ ጥቅም የቆመ፣ ሀገራዊ አንድነትን ያስቀደመ መንግሥት እንፈልጋለን” ያሉት አቶ ካሳ የዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብትን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቀዋል። ሰላም ሲሰፍን የማይወዱ፣ በሕዝብ ደም የሚነግዱ በውስጥ የተሰገሰጉ አካላትን መንግሥት በመመንጠር የሕዝብን ጥቅም ያስቀደሙ የሥራ ኀላፊዎች ወደ ፊት ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ፍሬህይወት እንደሻው አዲሱ የሚመሰረተው መንግሥት የተረጋጋች እና ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የተናገረው። እየተንሰራፋ የመጣው የሥራ አጥነት እና የኑሮ ወድነት ችግርም ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባ ነው የተናገሩት።
አቶ ሰኢድ አሰፋ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከምንም በላይ የሀገርን ሰላም በማስፈን የሕዝቦችን ደኅንነት ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ነግረውናል። የተፈናቀሉ ዜጎችንም ወደ ቀያቸው በመመለስ መደበኛ ህይወታቸውን እንዲኖሩ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ይህ ካልሆነ ችግሩ ከተፈናቀለው ሕዝብ ባለፈ ወደ ሌላው ሕዝብም ሊሰፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ላይ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።
ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት የሱፍ አሕመድ እንዳለው የሚመሠረተው መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። የሀገሪቱ አንቀሳቃሽ የሆነውን አምራች የወጣቱ ክፍል የሥራ ዕድል ሊፈጠርለት እንደሚገባም አንስቷል።
አሸባሪው እና ወራሪውን የትህነግ ቡድን በመደምሰስ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲኖሩ የማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አንስተዋል።
በአሸባሪው ቡድን የወደሙ መሠረተ ልማቶችም መልሶ በማቋቋም የመደበኛ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ-ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ