የልጃቸውን የ40 ቀን መታሰቢያ ወጪ ለተፈናቃይ ወገኖች ማዕድ በማጋራት ያወሉት ቤተሰብ…

359
ደባርቅ: መስከረም 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ነዋሪው ለሀገር ሲል በጦር ግንባር የተሰዋ ልጃቸውን የ40 ቀን መታሰቢያ ወጪ በደባርቅ ከተማ በመገኘት ለተፈናቃዮች ማዕድ በማጋራት አውለውታል።
በጋይንት ግንባር ልጃቸው የተሰዋባቸው አባትና ቤተሰቦቻቸው የልጃቸውን የ40 ቀን መታሰቢያ ወጪ በአሸባሪው ትህነግ ወረራ በደባርቅ ከተማ የተጠለሉ ወገኖች ማዕድ በማጋራት አስበዋል።
የ40 ቀን መታሰቢያ የተደረገለት ሕርያቆስ አበበ በጋይንት ግንባር በተደረገው ጦርነት ነበር በጀግንነት የተሰዋው። የአርባ ቀን መታሰቢያውን ከተፈናቃዮች ጋር ያሰለፉት የሕርያቆስ አባት አበበ ላቀው የ40 ቀን መታሰቢያ ለፅድቅ ነውና እገዛ በተለያየ መንገድ ከሚያገኙ ነዳያን ይልቅ ተፈናቅለው ለመጡ፣ ጎጇቸው ለፈረሰባቸው ማድረግ ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ማዕድ ማጋራታቸውን ተናግረዋል።
ያጣን ማብላት ለነብስ ጠቀሜታ ስላለው የተፈናቀሉ ወገኖችን ማዕድ ማጋራት እንዳስፈለጋቸውም ገልጸዋል።
ለተቸገሩትና ላጡት ሰዎች በማብላታችን በስጋ ደስ ብሎናል፣ በነብስም ይጠቅመናል ነው ያሉት።
ስጡ እሰጣችኋለሁ እንደተባለ ለተቸገሩት መስጠት ይገባል ነው ያሉት። ከሞቀ ጎጇቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሁሉም ካለው እያካፈለ ሊያግዛቸው ይገባልም ብለዋል።
❝ሰው ሰጥቶ አያጠግብም፣ መክተቻው ጎጆ ነውና ሁሉም በመረባረብ ወደ ጎጇቸው ሊመልሳቸውና ሊያቋቀማቸው ይገባል❞ ነው ያሉት።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ ዘርፌ ከፍያለው በአሸባሪው ትህነግ እኩይ ክፋት ሁለት ጊዜ መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ለሥራ ከሄዱበት ከመቀሌና በመቀጠል መኖሪያዬ ብለው ከተቀመጡበት ከጠለምት ነው የተፈናቀሉት። በደባርቅ ከተማ ከተጠለሉ ጀምሮ በወጣቶች አማካኝነት ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆዬታቸውንም ተናግረዋል። የልጃቸውን መታሰቢያ ወጪ ማዕድ ካጋሯቸው ቤተሰቦች ጋር በማሳለፋቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።
በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መንግሥት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
አቶ ነጋ ገብረ መድኅንም የተደረገላቸው የማዕድ ማጋራት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። በጎ አድራጊ ማኅበራት እና መንግሥት ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለደባርቅ ሕዝብ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የደባርቅና አካባቢው ሕዝብ ጠላትን በመመለስና የተፈናቀሉ ዜጎችን በመንከባከብ ታላቅ ተግባር መፈፀማቸውን ነው የተናገሩት። በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች በመደራጀት ጠላትን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ጠላትን እንደምናሸንፈውም እርግጠኞች ነን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በመደጋገፍ ነው የቆመችው፣ ከጎንደር ደባርቅ ድረስ መታሰቢያን አምጥቶ ሺዎችን መመገብ የሚመሰገን ነው ብለዋል። ለእኛ የሚያዝንና ስለ እኛ እንቅልፍ የማይወስደው ሰው መኖሩን አይተናል ነው ያሉት። መልካም ትውልድ ቢኖር ነው ይህን ማሰብ የተቻለውም ብለዋል።
የደባርቅ ወጣቶች በጎ ፈቃደኛ ማኅበር ፈንድ አፈላላጊና የሕዝብ ግንኙነት መሠረት ግዛት ተፈናቃዮች ማንም ባልደረሰላቸው ወቅት ከማኅበረሰቡ ምግብ እየለመኑ ይመግቧቸው እንደነበር ገልጿል። ወጣቶቹ ከተለያዩ አካላት ጋር በመገናኘት ደጋፊ እንዲኖር መሥራታቸውንም ተናግሯል። ወጣቶቹ ከበጎ ፈቃድ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሰጣቸውን ስጦታ ለተፈናቃዮች እያቀረቡ መሆኑን ነው የተናገረው።
ለተፈናቃዮቹ ቋሚ መጠለያ ስለሌላቸው አሁን ላይ ያሉበት መጠለያ ለሌላ አገልግሎት ሲፈለግ ተፈናቃዮች ለችግር ከመዳረጋቸው በፊት መንግሥት እንዲሠራም ነው የጠየቀው።
ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚቀጥሉም ተናግሯል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ባለቤቴን ማክሰኞ ገድለውት እስከ ቅዳሜ አልጋ ላይ አስተኝቼ ሰነበትኩ❞ ባለቤታቸውና ልጃቸው በአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተገደሉባቸው እናት
Next articleአዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ እንደሚገባ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።