ለዘማች ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

169
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን የከፈተውን ወረራ ለመመከት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ በርካታ የሚሊሻ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ዘመቻውን ተቀላቅለዋል፡፡ በግንባር የተሰለፈው የፀጥታ ኀይል የሽብርተኛው ትህነግን ወራሪ ቡድን በመደምሰስ ሀገርን ከብተና በመታደግ አኩሪ ገድል እየፈጸመ ነው፡፡ ሕዝቡም የህልውና ዘመቻውን በሙሉ መንፈስ በመቀላቀል ለዘማቹ እውነታኛ ደጀን ከመሆን ባሻገር ለዘማች ቤተሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሞጣ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ለሚገኙ 47 የዘማች ቤተሰብ አባላት የትምህርት ቁሳቁስ፣ አልባሳት እና ልዩ ልዩ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ገዳሙ መኮንን አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድንን ለመደምሰስ በግንባር ለተሠለፉ የፀጥታ አባላት ልጆቻቸው በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኀላፊው ጽሕፈት ቤቱ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ የዘማች ቤተሰቦችን ብቻ ሳይሆን ለ80 ተፈናቃይ ተማሪዎችም የአንድ ዓመት ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ለማስተማር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርሃኑ ዋለ በወረዳው ወላጆቻቸው ወደ ግንባር የዘመቱ 306 ተማሪዎች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሸፍኑ በወረዳ ደረጃ ሥምምነት ላይ መደረሱን አብራርተዋል፡፡ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነጻ እንዲመዘገቡም ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው በወረዳው የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ማኅበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጋዥ በማድረግ ተማሪዎቹ ያለምንም ችግር እንዲማሩ ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባሻገር የ300 ተፈናቃይ ተማሪዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ለማስተማር ከወረዳ አስተዳደሩ ጋር ሥምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስለሽ ተመስገን በዞኑ የዘማች ሚሊሻ አባላት ተማሪ ልጆች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቂ የመማሪያ ቁሳቁስ የማቅረቡ ሥራው ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹን በተገቢው ሁኔታ ለማስተማር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ስለሽ ከሚሊሻ ቤተሰቦች ጎን ለጎን ተፈናቃይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዞኑ በገባው ቃል መሠረት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን 962 የመጀመሪያ ደረጃ፣ 71 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እየሠጡ ነው ያሉት ኀላፊው እያንዳንዱ ወረዳ ምን ያህል ተፈናቃይ ተማሪዎችን ለማስተማር አቅም እንዳለው በምክር ቤት ደረጃ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ስለሽ በዞኑ የመማሪያ ክፍል ሆነ የሚያስተምሩ መምህራን እጥረት እንደማይገጥም ተናግረዋል፡፡ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ለማስተማር በሚደረገው ርብርብ ማኅበረሰቡን የማወያየት ሥራ መሠራቱንም ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሥራው በአግባቡ እንዲከናወን በሚደረገው ርብርብ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ መስከረም 17/2014 ዓ.ም ዕትም
Next article❝ባለቤቴን ማክሰኞ ገድለውት እስከ ቅዳሜ አልጋ ላይ አስተኝቼ ሰነበትኩ❞ ባለቤታቸውና ልጃቸው በአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተገደሉባቸው እናት