“የእነሱ ትልቁ ኀይል ዘር ሲሆን የእኛ ትልቁ ሞተራችን ኢትጵያዊነት ነው…” የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ

779
ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ አሸባሪው ትህነግ ከጦርነቱ በፊት የእሱን ጥቅም በኢትዮጵያ ላይ መጫን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ካለ አብሮ ለመሥራትና የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት በጉልበት በመጠምዘዝ የራሱን ፍላጎት ማሟላት ከጀርባ ይዞት የነበረው ዓላማ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ይሄ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን ማፍረስ ዓልሞ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል አበባው እንገለጹት የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አባላት ለዚህ ዓላማቸው መሳካት ወታደር ያስፈልገናል ብለው ልዩ ኀይልን እንደ ሽፋን ተጠቅመው ከ200 ሺህ በላይ የሰው ኀይል አደራጅተው ነበር፤ ጦርነት የጀመሩት፣ ዓላማውም ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፤ እኛ ደግሞ የተከተል ነው ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ከብተና የማዳን ነው፤ የጦርነቱ ፍትሐዊነት የሚመነጨውም ከዚህ ነው ብለዋል፡፡
በህግ ማስከበር ዘመቻው የጦርነቱን ዋነኛ ማዕከል መቀሌን አድርገን በፍጥነት በመሄድ ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ መቀሌን መቆጣጠር አለብን፤ ካልሆነ አደጋ ነው ብለን አንድ ሰው እንደ አስር እየተዋጋ በፍጥነት ጨርሰናል ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል አበባው፡፡ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በሰው ኀይል ማደራጀት ሽብርተኛው ትህነግ የበላይነት እንደነበረው የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል አበባው ነገር ግን “የእነሱ ትልቁ ኀይል ዘር ሲሆን የእኛ ትልቁ ሞተራችን ኢትጵያዊነት ነው” ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያዊነቱ መንፈስ እንደገና ደግሞ ዩኒፎርም ለብሰህ ዩኒፎርም የለበሰ ጓደኛህ ከኋላህ ሲመታህ የሚፈጥረው መንፈስ አለ፤ ያንን ጉልበት ይዘን ነው የተዋጋነው፡፡ ከሠራዊት አንጻር ያስቀመጥነውን ግብ አሳክተናል፤ የታገቱብንን አባሎቻችንን አስለቅቀናል፤ የተወሰዱብንን ብረትና ተተኳሽ አስመልሰናል፤ ኢትዮጵያን አድነናል” ነው ያሉት፡፡
ሌተናል ጄኔራል አበባው ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የነበረው ሽብርተኛው ትህነግ አስኳል መበታተኑንና የሚደመሰሰው መደምሰሱን አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ሁሌም የሚወጋት የእኛ የራሳችን ሰው ከውጭ ኀይል ጋር በመሆን ነው ብለዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል አበባው እንዳሉት የውጭ ኀይል ቀጥታ አይመጣም፤ የውስጥ ሰውን እየያዘ ነው እየተዋጋን ያለው፤ ከውጭ የሚመጣው ጠላት በግልጽ ቢመጣማ ኖሮ ምንም ችግር አልነበረም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሰው የፈለገውን አስተሳሰብ፣ የትኛውንም እምነት ይከተል፤ የትኛውንም ፖለቲካ ይከተል እኛ አያገባንም፤ ኢትዮጵያን ከነኩ ግን ከውጭ ሰው ሳይሆን የምንጀምረው ከራሱ ነው፤ የራሳችንን ቤት ቆሻሻ ካላጸዳን ኢትዮጵያን ማቆም አንችልም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሠራዊቱ እየተጠናከረ መሆኑን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል አበባው በትጥቅ፣ በአየር ኃይል፣ በእግረኛ ኃይል፣ ሊገመት በማይችል አይነት መልኩ ነው እየተዘጋጀ ያለው ብለዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱን ማጠናከር ለማንኛው ኢትዮጵያዊ በሩ ክፍት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
እንደ ሌተናል ጄኔራል አበባው ማብራሪያ ማንም ሰው መከላከያን መቀላቀል ይችላል፤ መደገፍ ይችላል፤ ማረም ይችላል፤ ምክንያቱም የራሱ ሀብት ነው፤ የውስጥ እና የውጭ ስጋት አለብን፤ የውስጥ ስጋቱ ጊዜ የሚፈጅ አይደለም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚስተካከል ነው፤ ለውጭው ስጋት ጠንክረን መዘጋጀት አለብን፡፡
በሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፍጹም ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀየር ነው ሌተናል ጄኔራል አበባው ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የጠቆሙት፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ይሄ ጊዜ መለማመጃችን ይሆናል” ያሉትን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል አበባው “እኛ የሚያስፈልገን ዘር አይደለም፤ ሰውነታችን ነው፤ ሰውነታችን ካለ ሀገር አለ” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየእንባ ሌቦች…
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።