የእንባ ሌቦች…

297

ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በማይካድራ በማንነት አማራን ጨፍጭፎ አርፎ አልተቀመጠም፡፡ የማይካድራ እናቶችን እና ሕጻናትን እንባ መስረቅ ጀመረ እንጂ፡፡ ይህ እንባ የመስረቅ ደባ ተራ ሌብነት አይደለም፡፡ ሌብነቱ ቀደም ባሉ ጊዜያትም ነበር፡፡ አሸባሪው ቡድን አራት ኪሎ ከገባ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮም ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በሕዝብ አመጽ እስኪወገድ ድረስ ራሱን የቻለ ወረርሽኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ስለ ደርግ ሁሉንም ወገን የሚያስማማ አንድ ነገር ቢኖር ሌብነት እንደሀገር የተዳከመበት ጊዜ ነበር፡፡ ደርግ በብዙ ነገር ይወቀሳል፤ በሌብነት ግን በጠላቶቻቸው እንኳ አይታሙም ይባል ነበር፡፡ የደርግ ባለስልጣናት ቀን ተሰብስበው የወሰኑትን ማታ በቴሌቪዥን ለማየት የቀበሌ መዝናኛ ክበብ የሚቀመጡበት ዘመን እንደነበርም ይነገራል፡፡ ለምን ቢሉ በወቅቱ ባለስልጣናቱ ደመወዛቸው ቴሌቪዥን ለመግዛት አይበቃቸውም ነበርና፡፡ በላኪዎቻቸው ታዝለው አራት ኪሎ የደረሱት የትህነግ ወንበዴዎች የመንግሥቱ ኃይለማርያምን አልጋ ሲመለከቱ ካሰቡት ውጭ ሆኖ አገኙት፡፡ “የጠፍር አልጋ ላይ ነበር የቀድሞ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሚተኙት” ማለታቸውንም ታሪክ ያትታል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚዘምረው አሸባሪው ትህነግ በትክክል አብዮታዊ ለውጥ ያመጣው ስርቆትን በማዘመን ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ያለ ሕዝብ ይሁንታ በጉልበት ከጎንደር እና ወሎ ለም መሬቶችን በመስረቅ፡፡ አሸባሪው ትህነግ በዘመነ ስልጣኑ ያልሰረቀውና ያልዘረፈው ነገር የለም፡፡

ኢትዮጵያ ሕንጻ እንደ ሾላ ብቻውን በቅሎ “ባለቤቱ የት ነው?” እየተባለ የተፈለገባት ሀገር ናት፣ ይህም የአሸባሪውን ትህነግ የሌብነት ጥግ ያሳያል፡፡ ተራራ የተሰረቀባት ብቸኛዋ ሀገርም ናት- ኢትዮጵያ፡፡ ራስ ዳሸንን ያክል ተራራ ፈልሶ ትግራይ የገባበትን ካርታ ማን ሊረሳ ይችላል? ተራራውን እና መሬቱን ብቻ አይደለም አሸባሪው ትህነግ የሰረቀው፤ ታሪክንም ለመስረቅ ጥሯል፡፡

አሁን ደግሞ እንባችንን እየሰረቀ ነው፡፡ በአማራ ጥላቻ የሰከረው አሸባሪው ትህነግ በማይካድራ ሰዎችን በአማራነታቸው ለይቶ በጅምላ ከፈጀ በኋላ አርፎ አልተቀመጠም፡፡ የማይካድራ እናቶችን እና ሕጻናትን እንባ ነው መስረቅ የጀመረው፡፡ ይህ እንባ የመስረቅ ደባ ተራ ሌብነት አይደለም፡፡ ፈረንጆች “ሺፍቲንግ ዘ ብሌም ወይም ብሌሚንግ ዘ ቪክቲም” ይሉታል፡፡ በአንድ አካል ላይ ግፍ ከሠራህ በኋላ ለሠራኸው ግፍ ተጠያቂ መሆን አትሻም፡፡ ስለዚህ የሠራኸውን ግፍ መካድ ብቻ አይደለም፡፡ ጭራሽ መቶ ሰማኒያ ድግሪ ዙረህ ግፍ የፈጸምክበትን ሰው ትከሰዋለህ፡፡ በትክክል የሰራህበትን ግፍ በኔ ላይ ፈጸመብኝ ብለህ ትጮሃለህ፡፡ በጅምላ ገድለህ እጅህ ላይ ያለው ደም ሳይደርቅ ድንኳንህን ጥለህ “አለቅሁ፤ ተፈጀሁ፤ የዘር ፍጅት ተፈጸመብኝ” እያልክ እሪታህን ታቀልጣለህ፡፡ ግፍ የፈጸምክበትን ሰው እንባ ሰርቀህ ታለቅሳለህ፡፡ ይህን ግፍ ከፈጸምክ በኋላ የራስህን ወንጀል በሌላው የማላከክ፣ ከዚህ አለፍ ሲልም ግፍ የፈጸምክበትን መልሰህ ተጠያቂ በማድረግ ሌብነቱን ከፍ ታደርገዋለህ፡፡May be an image of 4 people and people sitting

ይህ ስልት ከሥነ ልቦና አንጻር ጠላትን ግራ ለማጋባት እራሱን እንዲጠራጠር ለማድረግ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እራስህ አቁስለኸው መልሰህ ያንኑ አካል አቁስሎኛል ብለህ ስትከሰው ሁሉ ነገር ይምታታበታል፡፡ ራሱን የመጠራጠር የአዕምሮ ጤናውን የመጠየቅ ድባብ ውስጥ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ባላንጣን የማሳበድ ስልት ይሉታል፡፡ ይህ ስልት ግፍ የሰራህበትን ሰው ጩኸቱን ሰርቀህ እምባውን ቀምተህ ለራስህ ጥፋት እሱን መልሰህ የምታስጠይቅበት እጅግ ሰይጣናዊ ተንኮል ነው፡፡

አሸባሪው ትህነግ ሁለቱንም ስልቶች በተለይ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሰፊው ተጠቅሟል፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ ላይ ቃታ ከሳበ በኋላ መልሶ መከላከያ ሠራዊትን በአጥቂነት ለመክሰስ ሞክሯል፡፡

በማይካድራ ንጹሃንን በማንነታቸው ለይቶ በጅምላ በመፍጀት መልሶ በማይካድራ በጅምላ የተገደሉት ትግረኛ ተናጋሪዎች ናቸው በማለት ወንጅሏል፡፡ በአፋር ጋሊኮማ ሴቶች እና ሕጻናትን በከባድ መሳሪያ ከፈጀ በኋላ የራሱን ወንጀል በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የማላከክ ስልትን ተግብሯል፡፡No photo description available.

በወሎ አጋምሳ፣ በጎንደር ጭና ተክለሃይማኖት ለፈጸመው የጅምላ ፍጅት ሁሉ ሌላውን አካል ለመወንጀል ጥሯል፡፡ በታላላቅ ሃይማኖታዊ ተቋማት ቅርሶች ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ መልሶ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከሷል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ አስገድዶ ደፍሯል፤ ገድሏ፤ ጨፍጭፎ ሲያበቃ መልሶ ሌላውን ወንጅሏል፡፡

“ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉ አሸባሪው ትህነግ ወንጀለኛው ራሱ ሆኖ ሳለ ሌላውን የመክሰስ ስልት አስገራሚ ባይሆንም ዘመቻው በታላላቅ ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እና በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ሁሉ መስተጋባቱ ጉዳዩን እጅግ አደገኛ ያደርገዋል፡፡

ትናንት እህትህን እና እናትህን ያሳጣህ ነፍሰ በላ ቡድን ራሱ ተጠያቂ መሆን ሲኖርበት ገልብጦ በዓለም አደባባይ ለማስፈረድ ሲጥር ጠንካራ የአጸፋ መልስ ያስፈልጋል፡፡ የትናንት መዘናጋቶች ዛሬ ከፊታችን እንደጠበቁን ሁሉ የዛሬ ዝምታም ነገ ሌላ ችግር ቋጥሮ እንዳይጠብቀን፣ አሸባሪው ቡድንም የሥራውን እንዲያገኝ ከወዲሁ መትጋት ግድ ይላል፡፡ ይህን ማሸነፍ የሚቻለውም ግፎችን መዝግቦና ሰንዶ ለዓለም ሕዝብ በተገቢው መንገድ በማሳወቅ አስቀድሞ መታገል እና መሟገት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በዮሐንስ ልጅዓለም

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየመስቀል በዓልን አስመልክቶ የጎንደር ከተማ አስተዳደር እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኀላፊዎች ለህልውና ዘመቻው የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው፡፡
Next article“የእነሱ ትልቁ ኀይል ዘር ሲሆን የእኛ ትልቁ ሞተራችን ኢትጵያዊነት ነው…” የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ